ሮናልዶ በሳኡዲ ሊግ የፈጠረው መነቃቃት ምን ይመስላል?
ሊጉ በአሁኑ ወቅት በ140 ሀገራት ይሰራጫል፤ ከቴሌቪዥን ስርጭቱ የሚገኘው ገቢም በ650 በመቶ መመንደጉ ተገልጿል
የሳኡዲ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆኑም ንግግር መጀመሩ ተነግሯል
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ሳኡዲው አል ናስር ክለብ መዛወሩ ክለቡን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሳኡዲ ፕሮ ሊግን ገቢ እያሳደገ ነው።
ሮናልዶ ወደ ሳኡዲ ሲገባ የሳኡዲን ሊግ የሚያስተላልፉ ሀገራት ቁጥር ወደ 140 አድጓል።
ከቴሌቪዥን ስርጭት የሚገኘው ገቢም በ650 በመቶ መመንደጉን ነው የሊጉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ካርሎ ኖህራ ለብሉምበርግ የተናገሩት።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት 650 ሚሊየን ዶላር አውጥተው ተጫዋቾችን ያስፈረሙት የሳኡዲ ክለቦች በ2023/24 የውድድር አመትም ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብለዋል።
ካሪም ቤንዜማን ከሪያል ማድሪድ፤ ኔይማርን ከፒኤስጂ፤ ጆርዳን ሄንደርሰንን ከሊቨርፑል ያስፈረሙት የሳኡዲ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ እድል እንዲያገኙ ንግግር ስለመጀመሩም ነው የገለጹት።
“የተለየ ሆኖ ለመቅረብ ጥረት እያደረግን ነው” ያሉት ካርሎ ኖህራ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የፎርማት ለውጥ ወይም ማሻሻያ አድርጎ የሳኡዲ ክለቦችን በሻምፒዮንስ ሊጉ እንዲያሳትፍ ጠይቀናል ሲሉ ተደምጠዋል።
ይሁን እንጂ የሳኡዲ ፕሮ ሊግ ክለቦች የእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸው በነበረበት እንደሚቀጥል በማንሳት።
የሀገሪቱ ክለቦች የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን በተመለከተ ንግግር የሚያደርጉት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና የሳኡዲ እግር ኳስ ፌደሬሽን ናቸው።
ማዕከላዊ እስያዊቷ ሀገር ካዛኪስታን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ክለቦቿ እንደሚጫወቱ ያታወቃል።
የሳኡዲ አረቢያ ክለቦችም ከ2025 ጀምሮ በሻምፒዮንስ ሊግ መወዳደር ይጀምራሉ በሚል ሲወጡ የነበሩ ዘገባዎችን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሀሰት ናቸው ማለቱ የሚታወስ ነው።