ኢራን ሮናልዶ ወደ ቴህራን ዳግም ከተመለሰ “99 ጊዜ ይገረፋል” መባሉን አስተባበለች
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች በመስከረም ወር በቴህራን በነበረው ቆይታ የስዕል ስጦታ ያበረከተችለትን እንስት ጉንጯን ስሟል በሚል ከኢራን ጠበቆች ክስ ቀርቦበታል
በኢራን ትዳር ውስጥ ያለ ወንድ ከሚስቱ ውጭ ሴት ልጅን ከነካ እንዳመነዘረ ይቆጠራል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዳግም የኢራንን ምድር ከረገጠ “99 ጊዜ ይገረፋል” በሚል እየወጡ የሚገኙ ዘገባዎች ሀሰት መሆናቸውን የቴህራን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የሳኡዲው ክለብ አል ናስር ተጫዋች በመስከረም ወር ቡድኑን እየመራ ወደ ኢራን ሲያመራ በቴህራን ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች አል ናስር በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ የኢራኑን ፐርሴፖሊስ ከመግጠሙ በፊትም ሆነ በኋላ ከበርካታ ኢራናውያን ጋር የተገናኘ ሲሆን ስጦታም ተዥጎድጉዶለታል።
በዊልቼር የምትሄደው ሰአሊ ፋጢማ ሃሚሚ በእግሯ የሳለችውን የሮናልዶን ምስል ለተጫዋቹ ማበርከቷ የበርካታ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት መሳቡ ይታወሳል።
ሮናልዶ ለተበረከተለት ስጦታ ሃሚሚን አቅፎ ጉንጯን በመሳም ፍቅርና አድናቆቱን መግለጹም አይዘነጋም።
ይህ ሁኔታም የተወሰኑ የኢራን ጠበቆችን አስቆጥቶ በሮናልዶ ላይ ክስ እስከመመስረት አድርሷቸዋል ነው ያለው የስፔኑ ተነባቢ ጋዜጣ ሙንዶ ዲፖርቲቮ።
በኢራን ትዳር የመሰረተ ወንድ ከሚስቱ ውጭ ሌላ ሴትን ከነካ እንዳማነዘረ ተቆጥሮ ቅጣት ይተላለፍበታል።
የኢራኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሻርቅ ኢምሮዝ ተጫዋቹ ወደ ኢራን ከተመለሰ “99 ጊዜ እንደሚገረፍ ተወስኗል፤ ውሳኔውም ለተጫዋቹ ደርሶታል” የሚል ዘገባ ማውጣቱ ነው የተሰማው።
ሌላኛው የስፔን ጋዜጣ ማርካ ግን ሮናልዶ በተፈጠረው ነገር መጸጸቱን ከገለጸ ውሳኔው ተፈጻሚ እንደማይሆን ዘግቧል።
ኢራን ግን የአምስት ጊዜ የባሎንዶር ተሸላሚው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በቴህራን “99 ግርፋት ይጠብቀዋል” በሚል እየወጡ ያሉ ዘገባዎችን አስተባብላለች።
በስፔን የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ “ሮናልዶ ከፋጢማ ሃማሚ ጋር ሲገናኝ ያሳየው ሰብአዊ ፍቅር በኢራናውያን እና በመላው የስፖርት ቤተሰብ የተወደሰ ነው” ብሏል።
ኢራን እንደ ሮናልዶ ባሉ አለማቀፍ ስፖርተኞች ላይ መሰል ውሳኔ አታስተላልፍም በሚልም ዘገባዎቹን ውድቅ አድርጓል።