ሮናልዶ ኤሪክ ቴን ሃግን በተቸበት ንግግሩ ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ እጣ ፈንታ ምን አለ?
ባለፈው የውድድር ዘመን መጥፎ ጌዜ ያሳለፉት ቴንሀግ በአዲሱ የውድድር ዘመን በደረሰባቸው ሁለት ሽንፈቶች በጫና ውስጥ ይገኛሉ
የቀድሞው የቡድኑ ተጫዋች ሮናልዶ አሰልጣኙ የቡድኑን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ትክክለኛው ሰው አይደሉም ብሏል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ማንችስተር ዩናይትድ እንደ ቡድን ደጋሚ እራሱን ማዋቀር ካልቻለ ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ እንደሚቸገር ተናገረ።
የአምስት ጊዜ ባላንዶር አሸናፊው ፖርቹጋላዊው ኮከብ ሮናልዶ ዩናይትድ እንደ ቀደመው በትላልቅ ውድድሮች ላይ ተፎካካሪ መሆን ከፈለገ ከአስተዳደር ጀምሮ እስከ አሰልጣኝ እንዲሁም ቡድን ግንባታ ላይ ድጋሚ ሊዋቀር ይገባል ብሏል።
ባለፈው የውድድር ዘመን 8ተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው እንዲሁም በአዲሱ የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 3 ጨዋታዎች ሁለቱን የተሸነፈውን ቡድን እየመሩ የሚገኙት ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ።
የቡድኑ አመራር ቴን ሀግ ቡድኑ አስፈላጊውን ውጤት እንዲያስመዘግብ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ሀላፊዎቹም የአሰልጣኙን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
ሆኖም ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የሚሰሙ ጭምጭምታዎች አሰልጣኙ ይህ አመት እስኪጠናቀቅ ድረስ ዩናይትድን ወደ ተፎካካሪነት መቀየር የማይችሉ ከሆነ ከሀላፊነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ የሚያመላክቱ ናቸው።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቴን ሀግ ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉም ሆነ በሻምፒዮንስ ሊግ መፎካከር አይችልም ሲሉ መናገራቸውን ጠቅሶ ይህ ትክክለኛ የአሰልጣኝ ስነልቦና አይደለም ብሏል።
“የትኛውም አሰልጣኝ በቡድኑ ውስጥ ድክመት እንዳለ እያወቀ እንኳን ቢሆን የቡድኑን አሸናፊነት ስሜት የሚያነሳሳ ማንኛውንም መስዕዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለበት ቴን ሀግ ለዚህ ትክክለኛው ሰው ናቸው ብየ አላምንም” ሲል ተናግሯል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የቀድሞው የክለቡ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከክለቡ ከለቀቁበት 2013 በኋላ በኦልትራፎርድ ምንም አይነት ወሳኝ ለውጥ አለመደረጉን አንስቷል።
ዩናይትድ አሁንም ከአለም ምርጥ ቡድኖች መካከል እንደሆነ የሚናገረው ተጫዋቹ ከመሰረተ ልማት ጀምሮ አስተዳደሮችን እና በአሰልጣኝነት ስፍራ ላይ የሚገኙ ሰራተኞቹን ሊፈትሽ እንደሚገባ ነው የተናገረው።
የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ሮይ ቫኒስትሮይ ቴን ሀግን ለማገዝ ወደ ቡድኑ በመምጣቱ ደስተኛ እንደሆነ ተናግሮ አሰልጣኙ ቡድኑን በደንብ የሚያውቁትን እንደ ቫኒስትሮይ ያሉ ሰዎችን ማድመጥ ቢችሉ መልካም ነው ብሏል።
በ2009 ወደ ሪያል ማድሪድ ከመዘዋወሩ በፊት በመጀመርያው ዙር ከክለቡ ጋር በነበረው የ6 አመታት ቆይታ ሮናልዶ ሶስት የፕርሚየር ሊግ ፣ ሁለት የሊግ ካፕ ፣ ሻምፒዮንስ ሊግ ፣ ኤፍኤ ካፕ ዋንጫዎችን እና ሌሎች ክብሮችን ማሳካት ችሏል።
ከጁቬንቱስ ድጋሚ በ2021 ቡድኑን ድጋሚ ከተቀላቀለ በኋላም በ346 ጨዋታዎች 145 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
በአሁኑ ወቅት በሳኡዲ አረብያው አልናስር እየተጫወተ የሚገኝው ሮናልዶ በእግር ኳስ ህይወቱ 901 ግቦችን በማስቆጠር የመጀመርያው ሰው ነው።