የሩሲያ እርምጃ ካናዳ በሩሲያዊያን ታዋቂ ሰዎች ላይ ለጣለችው ማዕቀብ ቀጥተኛ ምላሽ ነው ተብሏል
ሩሲያ 200 ታዋቂ የካናዳ ሰዎች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ማገዷ የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ካናዳ ቀደም ሲል በ33 የአሁን ወይም የቀድሞ የሩሲያ ባለስልጣናት እና በዩክሬን ያለውን ጦርነት በተቃወሙ ዜጎች ላይ "ስልታዊ የሰብአዊ መብት ረገጣ" በተሳተፉ ስድስት አካላት ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው፡፡
የአሁኑ የሩሲያ እርምጃ ካናዳ በሩሲያዊያን ታዋቂ ሰዎች ላይ ለጣለችው ማዕቀብ ቀጥተኛ ምላሽ ነው ተብሏል።
ሚኒስቴሩ በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ "በኦታዋ ለተጣለው የግል ማዕቀብ ምላሽ 200 የካናዳ ዜጐች በተመሳሳይ መርህ መሰረት እንዳይገቡ ተከልክለዋል" ብሏል፡፡
የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ካናዳ በ1 ሺህ 500 ሩሲያውያን፣ ዩክሬናውያን እና ቤላሩሲያን ላይ ማዕቀብ ጥላለች፡፡
ከካናዳ ጋር ያለው ግንኙነቷ እየሻከረ መምጣቱን የሚነገርላት ሞስኮ፤ አርብ እለት በሀገሪቱ የሚገኙትን የካናዳ አምባሳደር ጠርታ ማነጋገሯም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው የካናዳው አምባሳደር አሊሰን ሌክሌር፤ ኦታዋ "የሩሶፎቢክ ድባብን እየገፋች ነው እናም ከድርጊቷ ትቆጠብ" ተብሎ እንደተነገራቸውም አክሏል፡፡
በተያያዘ ካናዳ የኢራን የፍትህ አካላት ባለስልጣናትን ጨምሮ በኢራን፣ ሩሲያ እና በርማ በሚገኙ 67 ግለሰቦች እና 9 አካላት ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የካናዳ ባለስልጣናት እንደገለጹት ኮነ ማዕቀብ የተጣለባቸው አካላት “ከባድ እና ስልታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት” ፈጽመዋል በሚል ነው፡፡