ፕሬዝዳንት ባይደን የአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ሀገራት በፀጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ኢንዲሰጣቸው ጠየቁ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 77ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኒውዮርክ እየተካሄደ ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የተመድ የፀጥታው ም/ቤት የበለጠ አካታች ለማድረግ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቀዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ሀገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ኢንዲሰጣቸው ጠየቁ።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 77ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ባደረጉት ንግግር ነው ይህንን ጥያቄ ያነሱት።
ባይደን በንግግራራቸው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለአለም አቀፍ ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት የተሻለ ብቃት እንዲኖረው እና ሁሉንም አካታች እንዲሆን ለማድረግ ሪፎርም እንዲደረግበት ጥሪ አቅርበዋል
የፀጥታው ምክር ቤት አሁን ላይ 5 ቋሚ እና 10 ተለዋዋጭ በድምሩ 15 መቀመጫዎቸ ያሉት ሲሆን፤ ይህ የመቀመጫ ቁጥር እንዲጨምርም ፕሬዝዳንት ባይደን በንግግራቸው ጠይቀዋል።
በአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ውስጥ የሚገኙ ሀገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲያገኙ የጠየቁት ፕሬዝዳንት ባይደን፤ አሜሪካ ይህንን አቋም ለረጅም ጊዜ ስትደግፍ ቆይታለችም ብለዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላቸው ሀገራት በእነሱ ላይ ወይም በአጋሮቻቸው ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን የመሻር መብት አላቸው።
አሜሪካን ጨምሮ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላቸው ሀገራት ምክር ቤቱ ተዓማኒነት ያለው እና ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ከአቅም በላይ ከሆኑ ያልተለመዱ ሁኔታዎች ውጪ ድምጽን በድምጽ መሻር መብታቸውን ከመጠቀም እንዲቆጠቡም ባይደን አሳስበዋል።
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ለማስቻል የተለያዩ ዘመቻዎች እየተካሄዱ መሆኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም ይህንን የአፍሪካ ሀገራት በተመድ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለውን ሃሳብ መቀላቀላቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ እና የሴኔጋሉ አቻቸው ማኪ ሳል አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ማስታወቃቸውም አይዘነጋም።
የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርቶ ሙጋቤ አዲስ አበባ በፈረንጆቹ 2016 በተካሄደው 26ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ማሻሻያ እንዲያደርግ መጠየቃቸው ይታወሳል።