በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት በነገሰበት ጊዜ የተካሄደው ውይይት አጋርነትን የበለጠ ለማጠናከር ማለሙ ተነግሯል
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሩሲያ እና ኢራን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን 'በመተማመን' እያጠናከሩ መሆናቸውን አስታውቋል።
የሞስኮ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በቴህራን አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሀገራቱ በሁለትዮሽ አጀንዳዎችና አጠቃላይ የሩሲያ እና የኢራን አጋርነትን የበለጠ መገንባት ላይ ትኩረት በማድረግ በጥልቀት መወያየታቸውን ሞስኮ ገልጻለች።
የሰርጌይ ላቭሮቭ የእስያ ጉዟቸውን በቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ካደረጉ በኋላ ወደ ቴህራን ተጉዘው፤ ከኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴን አሚራብዶላሂን ጋር በኃይል እና ሎጀስቲክስ ዙሪያ ተወያይተዋል ተብሏል።
በመካከለኛው ምስራቅ እያሻቀበ ባለው ውጥረት ውስጥ የተካሄደው ንግግር ጥቂት ዝርዝሮች ብቻ ይፋ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ላቭሮቭ ኢራን ባስተናገደችው የአዘርባጃንና አርሜንያ ግጭት ዙሪያ በመከረው ክልላዊ ውይይት ላይም ተሳትፈዋል።
ሞስኮ የዩክሬን ጦርነት ከጀመረች ወዲህ የምዕራባዊያን ተገዳዳሪ ከሚባሉ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች ነው።
ዩክሬን ቴህራን ለሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) ማቅረቧን እንድታቆም በተደጋጋሚ አሳስባለች።
ኪየቭ ድሮኖቹ በዩክሬን ከተሞች እና መሰረተ ልማቶች ላይ ለደረሰው ጥቃት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ስትል ትናግራለች።