ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኢትዮ ቴሌኮም እየሰራበት ያለውን መንገድ አድንቋል
ሳፋሪኮም ኩባንያ በ2023 ዓመት ስራዎቹ ዙሪያ በኬንያ ናይሮቢ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የሳፋሪኮም ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ ፒተር ንዴግዋ እና የኩባንያው ኢትዮጵያ ቢሮ ስራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳ በጋራ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ለኤምፔሳ የሞባይል ፋይናንስ ፈቃድ መስጠቷን አድንቀዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይም የኢትዮጵያን ገበያ እየተቆጣጠረ ስላለው ቴሌብር ጋር እንዴት ልትፎካከሩ ትችላላችሁ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ገደብ መጣሉ፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የጥቅል አየር ሰዓት እና ኢንተርኔት መቼ ይጀምራል፣ ኤምፔሳ መቼ አገልግሎት ይጀምራል እና ሌሎችም ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ተነስተዋል።
የሳፋሪኮም ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ ፒተር ንዴግዋ በምላሻቸው እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌብር አማካኝነት ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሳፋሪኮም ንብረት የሆነው ኤምፔሳ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በማግኘታችን ስራችንን በቅርቡ እንጀምራለን ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌብር አማካኝነት የኢትዮጵያን ገበያ እየተቆጣጠረ ነው፣ ኤምፔሳ እንዴት ሊፎካከር ይችላል? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ ቴሌብር በኢትዮጵያ ጥሩ ስራዎችን እየሰራ ነው፣ የመንግስት ፍላጎት በውድድር ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ለህዝብ እንዲቀርብ ነው“ ብለዋል።
ኢትዮጵያ የፋይናንስ ፖሊሲዎቿን በየጊዜው እያሻሻለች መሆኑ ለኤምፔሳ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ደንበኞች ጥሩ እድል ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው ኢትዮጵጵያ ሰፊ እና ህዝቡም ገና ብዙ አገልግሎቶችን እያገኘ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ገበያ ሰፊ ነው፣ ልንወዳደርባቸው የምንችላቸው ብዙ አይነት አገልግሎቶች አሉ ሱሉ አክለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ዋነኛ ተፎካካሪያችን ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው የተሻሉ እና አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞቻችን መስጠት የሚያስችሉን አሰራሮች ይዘን እየመጣን ነውም ብለዋል።
አንዋር ሶሳ አክለውም የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ገደብ መጣሉ የማይካድ ነው፣ በደንበኞቻችን እና በእኛ ላይ ተጽዕኖ ማድረሱም ባይቀርም መንግስት ይህን ጉዳይ በቀጣይ እንደሚያስተካክለው ዕምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ደንበኞች የድምጽ እና ኢንተርኔት ዳታ ጥቅል አገልግሎት እንድናቀርብ ይጠይቁናል ያሉት ስራ አስፈጻሚው ዝግጅቶችን እያደረግን ነው በቀጣይ እናሳውቃለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኤምፔሳ በፈረንጆቹ 2007 ላይ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት በሚል በኬንያ የተመሰረተ ሲሆን አሁን ላይ ዓመታዊ የገንዘብ ልውውጡ 19 ቢሊዮን ዶላር ሲደርስ 51 ሚሊዮን ደንበኞችም አሉት።
ኬንያን ጨምሮ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ሌሴቶ፣ ታንዛኒያ፣ ጋና እና ሞዛምቢክ በመስራት ላይ ያለው ኤምፔሳ በቅርቡም የኢትዮጵያን ገበያ እንደሚቀላቀል ተገልጿል።