ሳኡዲ አረቢያ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ብቻ በተፈቀደ ስፍራ ገብቶ የተገኘ ጋዜጠኛን አሰረች
የታሰረው ግለሰብ የአሜሪካ ዜግነት ያለው እስራኤላዊ ጋዜጠኛ ነው ተብሏል
የእስራኤል መንግስት ድርጊቱን "ድድብና ነው" ሲል ድርጊቱን ኮንኗል
የእስራኤሉ ቻናል 13 የተሰኘው ሚዲያ ባሳለፍነው ሳምንት ሳኡዲ አረቢያ መካ መዲና ያካሄደችውን ሀይማኖታዊ በዓል አስመልክቶ ከስፍራው የቪዲዮ ዘገባ አሰራጭቷል።
ዘገባው አየር ላይ መዋሉን ተከትሎ በርካታ የእስልምና ተከታዮች ጋዜጠኛው እንዴት ለእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ብቻ ወደተፈቀደው ስፍራ እንዴት ሊገባ ቻለ ሲሉ ጠይቀዋል።
የሳውዲ ፖሊስም ዘገባውን በሰራው ጋዜጠኛ ላይ ባደረገው ማጣራት ግለሰቡ የአሜሪካ ዜግነት ያለው እስራኤላዊ ጋዜጠኛ እንደሆነ ደርሶበታል።
የሳኡዲ አረቢያ ፖሊስም ጋዜጠኛው የሀገሪቱን ህግ ጥሷል በሚል ክስ እንዲመሰረትበት ለሀገሪቱ አቃቢያነ ህጎች አሳልፎ ሰጥቶታል።
የእስራኤል አካባቢያዊ ትብብር ሚንስትር ኢሳዊ ፍሬጂ በበኩላቸው የጋዜጠኛውን ድርጊት ኮንነው "የተሰራው ስራ ድድብና እና ጎጂ ነው" ማለታቸው ተገልጿል።
ድርጊቱ እስራኤል ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሊጎዳ የሚችል እንደሆነም ሚንስትሩ አክለዋል።
የሳውዲ አረቢያ መንግስትም ይሄንን እና ሌሎች መሰል ወንጀሎችን እንደማይታገስ ገልጾ ማንኛውም ዜጋ የሀገሪቱን ህግ እንዲያከብሩ አስጠንቅቋል።