በሳኡዲ የቱሪዝም ሴክተሩ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ውስጥ ለ260,000 ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል
በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ማለትም እስከ 2030 መቶ ሚሊዮን ጎብኚዎችን ለመሳብ ውጥን መያዟን ሪያድ አስታውቃለች። ሪያድ እቅዷን ለማሳካት አንድ ትሪሊየን ዶላር መመደቧን ገልፍ እንሳይደር የተባለው የሳኡዲ አረቢያ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የሳዑዲ ምጣኔ ሐብት በዋናነት በነዳጅ ሐብት ላይ የተመሠረተ ነው።ነዳጅ የሃገሪቱ ምጣኔ ሐብት የጀርባ አጥንት ሆኖ ዓመታትን ዘልቋል።
አሁን ግን ምጣኔ ሐብታዊ አማራጮችን በማፈላለግ ከነዳጅ ጥገኝነት መላቀቅ የሳዑዲ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነው።
ለዚህም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ጎብኚዎችን በከፍተኛ ቁጥር ለመሳብ ታስቦ እየሰራ ነው።የሳኡዲ መንግስት ሀብቱ በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ መቶ ሚሊዮን ጎብኚዎችን ለመሳብ እንደሚያስችልም አምኖበታል፡፡
ልክ እንደ ሳዑዲ ሁሉ ሌሎቹም የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ምጣኔ ሃብትን ለመገንባት የሚያስችል ውጥን መያዛቸው ይታወቃል።
ሪያድ በልዑል አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የሚመራና እስከ 2030 የሚዘልቅ የአስር ዓመታት ሐገራዊ እቅድ ይፋ ማድረጓም የሚታወስ ነው።
ሳኡዲ አረቢያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በተደረጉ የጉዞ ገደቦች በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶቿ ተጎድተዋል፡፡ የአለም ኢኮኖሚ ማገገም በቱሪዝም ዘርፍ ማገገም ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሳኡዲ መንግስት ያምናል፡፡
የቱሪዝም ሴክተሩ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ውስጥ 260,000 ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ሲጠበቅ በ2030 አንድ ሚሊዮን የስራ እድል ለመፍጠር አልሟል፡፡ ሴክተሩ በአጠቃላይ ለ1.6 ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል ይፈጥሯል ተብሎ ይጠበቃል፡፡