የሳኡዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን የቱርኩን ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንን በጂዳ ተቀብለው አነጋገሩ
ኤርዶጋን ጉብኝቴ ሁለቱም ሀገራት አዲስ የትብብር ዘመን ለመጀመር ያላቸውን የጋራ ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብሏል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሳኡዲ አረቢያን ሲጎበኙ እንደፈረንጆቹ ከ2017 ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ጉብኝት መሆኑ ነው
የሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን የቱርኩን ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንን በጄዳ ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
መሀመድ ቢን ሳልማን እና ኤርዶጋን በሳኡዲ-ቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ የመከሩ ሲሆን ፤ በሁሉም ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር ማጎልበት የሚቻልባቸውን መንገዶች ገምግመዋል።
ኤርዶጋን “ጉብኝቴ እንደ ሁለቱ ወንድማማች ሀገራት አዲስ የትብብር ዘመን ለመጀመር ያላቸውን የጋራ ፍላጎት የሚያሳይ ነው”ብሏል፡፡
በፖለቲካ፣ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በባህል በሁሉም ጉዳዮች በሁለቱ ሀገራት መካከል የተሻሻለ ግንኙነት ለመጀመር ጥረቶችን እናደርጋለን ሲሉም አክሏል፡፡
የቱርክ ኮንትራክተሮች በሳውዲ አረቢያ 24 ቢልዮን ዶላር የሚገመት ኢንቨስትመንት አላቸው ያሉት ኤርዶጋን፤ የሳኡዲ አረቢያ ባለሃብቶች መዋእለ ነዋያቸውን በቱርክ ፈሰስ ሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ እንዳለም ጠቁሟል፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሀገራቱ ከንግድና ኢንቨስትመንት በዘለለ በርካታ በትብብር የሚሰሩባቸው መስኮች አሉም ብሏል፡፡
“ጤና፣ኢነርጂ፣ የምግብ ዋስትና፣ግብርና ቴክኖሎጂ፣ መከላከያ ኢንዱስተሪ እና ፋይናንስ ፤ ሀገራቱ በቀጣይ በትብብር ለመስራት የሚፈልጓቸው መሽኮች መሆናቸው”ም አስታውቋል፡፡መሪዎቹ ከሁለትዮሽ በዘለለ በቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም መክረዋል ተብለዋል፡፡
ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የሳኡዲው አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን ጋር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ በመካ ታላቁ መስጂድ ኡምራ ማድረጋቸውም ተገልጿል።የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን፤ ሳኡዲ አረቢያን ሲጎበኙ እንደፈረንጆቹ ከ2017 ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ጉብኝት መሆኑ ይታወቃል፡፡