የሶሪያ አማጺያን ሀማ የተባለችውን ስትራቴጂካዊ ከተማ ተቆጣጠሩ
የሶሪያ ጦር "የንጹሃንን ደህንነት ለመጠበቅ እና የከተማዋ ህዝብ በጦርነቱ እንዳይሳተፍ" ለማድረግ ሲል ከከተማዋ መውጣቱን አስታውቋል

የሶሪያ የእርስበርስ ጦርነት ከተጀመረበት ከ2011 ጀምሮ በሶሪያ ጦር ስር የነበረችውን የሀማ ከተማ ማጣት ለሶሪያ አገዛዝ ትልቅ ኪሳራ ነው ተብሏል
የሶሪያ አማጺያን ሀማ የተባለችውን ስትራቴጂካዊ ከተማ ተቆጣጠሩ።
የሶሪያ አማጺ ቡድኖች የሀገሪቱን ትልቅ ከተማ አሌፖን ከፕሬዝደንት በሽር አላሳድ ኃይሎች ካስለቀቁ ከቀናት በኋላ ሀማ የተባለችውን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ መቆጣጠር መቻላቸው ተዘግቧል።
የቀድሞ የአልቃ ኢዳ አጋር በሆነው ሀያት ታህሪር አልሻም(ኤችቲኤስ) የሚመሩት አማጺ ቡድኖች ከአላሳድ ኃይሎች ጋር ለቀናት ከተዋጉ በኋላ በትናንትናው እለት ሀማ ከተማ ገብተዋል።
ለአላሳድ ታማኝ የሆነው የሶሪያ ጦር "የንጹሃንን ደህንነት ለመጠበቅ እና የከተማዋ ህዝብ በጦርነቱ እንዳይሳተፍ" ለማድረግ ሲል ከከተማዋ መውጣቱን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤችፒኤስ መስራቹ አቡ መሀመድ አል ጎላኒ ባስተላለፈው የቪዲዮ መልእክት የአማጺያኑ ከተማዋን መያዝ ብቀላ ሳይሆን ምህረት መሆኑን ገልጿል።
የሶሪያ የእርስበርስ ጦርነት ከተጀመረበት ከ2011 ጀምሮ በሶሪያ ጦር ስር የነበረችውን የሀማ ከተማ ማጣት የሶሪያ አገዛዝ እና ድጋፍ ለሚያደርጉለት ሩሲያ እና ኢራን ትልቅ ኪሳራ ነው ተብሏል።
ሩሲያ ባደረገችው ከባድ የአየር ጥቃት በመታገዝ በ2016 አገዛዙ አሌፖን ከተቃዋሚዎች መንጠቅ ችሎ ነበር።
አማጺያኑ በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በመወሰናቸው ምክንያት ባለፉት አመታት ውጊያው ቆሞ ነበር። ነገርግን በህዳር ወር የመጨረሻ ሳምንት የተጀመረው መልሶ ማጥቃት ይህን ሁኔታ ቀይሮታል። ሀማ የበሽር አላሳድ አገዛዝን በመቃወም ረጅም ታሪክ አላት።
ሀማ የ1982ቱ አመጽ የተነሳባት እና የአሁኑ ፕሬዝደንት አባት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ ያደረጉባት ነች። አሁን ላይ አገዛዙ ወደ ደማስቆ መግቢያ በሆነችው እና ከሀማ በ25 ማይል ርቀት ላይ ወደምትገኘው የሀገሪቱ ሶስተኛ ትልቅ ከተማ ሆምስ ትኩረት ማድረጉ ተገልጿል።