ታዳጊዎች "መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ" የግዳጅ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጫለሁ -ኢሰመኮ
ኢሰመኮ ቤተሰቦቻቸው በግዳጅ የተያዘባቸው ሰዎች ገንዘብ እየከፈሉ እያስለቀቁ መሆኑንም ገልጿል
የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከ11 ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችን ከህግ ውጪ ለግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት እየመለመሉ ነውም ተብሏል
ታዳጊዎች "መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ" የግዳጅ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጫለሁ -ኢሰመኮ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት የመከላከያ ሰራዊት አባል ለመሆን የሚፈልጉ ዜጎችን ምልመላ አስመልክቶ ያደረገውን ምርመራ ይፋ አድርጓል፡፡
ከሚሽኑ ምርመራውን በኦሮሚያ ክልል በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙ እጩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ማቆያ ስፍራዎችን በመጎብኘት፤ በማቆያ ስፍራዎቹ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በጉዳዩ ዙሪያ ቃለ መጠይቅ ማድረጉን ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርም የመከላከያ ሰራዊት ምልመላ ሂደቱን በመከላከያ ሚኒስቴር መስፈርቶች መሠረት እንዲያከናውን መጠየቁን እንደተረዳ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ይሁንና የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር አካላት እና የጸጥታ ኃይሎች አባላት በመከላከያ ሚኒስቴር ከተገለጸው የምልመላ መስፈርት ውጪ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን “የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ” በሚል በግዳጅ እንደያዙ በዚህ ምርመራው እንዳረጋገጠ ኢሰመኮ ጠቅሷል፡፡
እንዲሁም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በዚህ አግባብ የተያዙ ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደዳቸውን ኢሰመኮ በምርመራዬ አረጋግጫለሁም ብሏል።
ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ባደረገባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ከክልሉ አመራሮች ጋር በመተባበር “የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ” በሚል ተይዘው የነበሩ ሕፃናትን እና የአእምሮ ሕሙማንን ጨምሮ በግዳጅ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ማስለቀቅ መቻሉንም ገልጿል።
በወቅቱ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ችግሩ መኖሩን እንዳመኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
የማቆያ ስፍራዎችን በመፈተሽ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆናቸውን እና ድርጊቱን በፈጸሙ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የሚሊሻ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ለኢሰመኮ ተናግረዋልም ተብሏል።
ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችም ከመስፈርት ውጪ የተደረገ ምልመላ መሆኑን በመግለጽ በክልሉ የጸጥታ አካላት የተያዙ ሰዎች ከማቆያ ስፍራዎች እየተለቀቀቁ መሆኑን ኢሰመኮ ገልጿል።
እንደ ኢሰመኮ ሪፖርት ከሆነ እድሜያቸው ከ11 ዓመት ጀምሮ ወደ መከላከያ ሰራዊት ለውትድርና አገልግሎት እንዲቀላቀሉ በመንገስት የጸጥታ ሀይሎች ተይዘዋልም ተብሏል፡፡
አንዳንድ የክልሉ ሚሊሻ አባላት ወጣቶችን ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት ምልመላ በሚል ከያዙ በኋላ ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ መሆኑን ኢሰመኮ አረጋግጫለሁም ብሏል።
ይህ ገንዘብ እንዲከፈል የማስገደድ ድርጊት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ሪፖርት የተደረገ ሲሆን በተለይም በአዳማ ከተማ እና አካባቢው ተስፋፍቶ ሲፈጸም እንደነበረ ተገልጿል።
ኢሰመኮ በክትትል እና ምርመራው የደረሰባቸውን ግኝቶች አስመልክቶ በወቅቱ ያነጋገራቸው የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ችግሩ መኖሩን የሚያውቁ መሆኑን እንደገለጹለት ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ካስቀመጠው መስፈርት ውጪ የተከናወኑ ምልመላዎች በአፋጣኝ እንዲታረሙ መመሪያ መሰጠቱን፤ በክልል አመራር ደረጃ ወደታችኛው አስተዳደር እርከን መዋቅር በመውረድ የምልምል ማቆያ ስፍራዎችን በመጎብኘት ያለፈቃዳቸው የተያዙ ሰዎች እየለቀቁ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችም መረጃውን መሠረት በማድረግ ከመስፈርት ውጪ የተመለመሉ ሰዎች ከማቆያ ስፍራዎች እንዲወጡ አድርገዋልም ተብሏል፡፡
በመሆኑም ከመስፈርቶች ውጪ ለወታደራዊ ምልመላ በሚል ሰዎችን በግዳጅ የያዙ፣ የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ የገንዘብ ክፍያ የጠየቁ፣ የተቀበሉ እና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት በህግ እንዲጠየቁ ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡