አቶ ታዬ ደንደዓ ከአንድ ዓመት እስር በኋላ ተለቀቁ
የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከሁለት ወራት እስር በኋላ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል

አቶ ታዬ ባለፈው ሰኞ በ20 ሺህ ብር ዋስትና ክሳቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤት መወሰኑ ይታወሳል
አቶ ታዬ ደንደዓ ከአንድ ዓመት እስር በኋላ ተለቀቁ፡፡
የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ታህሳስ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡
የጸጥታ እና ደህንነት ግብረ ሀይል በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አቶ ታዬ “ከኦነግ ሸኔ አመራሮችና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግስትን በአመጽ፣ በሽብርና፣ በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴር ተደርሶበታል“ ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ይህን ተከትሎም አቶ ታዬ ደንደዓ ከታሰሩ ከሁለት ወር በኋላ ማለትም የካቲት 2016 ዓ.ም በጨፌ ኦሮሚያ ያለ መከሰስ መብታቸው ተነስቷል፡፡
ይህን ተከትሎም የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ላይ በአቶ ታዬ ደንደዓ ላይ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እንዲሁም የጦር መሣሪያ ሕጉን በመተላለፍ በሚል በሶስት ወንጀሎች ክስ መስርቶባቸው ነበር።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ከዚህ ቀደም ከሦስቱ ክሶች መካከል በሁለቱ፣ ሁከት እና ብጥብት በማነሳሳት እና የፀረ- ሰላም ኃይሎችን ድጋፍ ማድረግ ክሶች በነጻ አሰናብቷቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የጦር መሣሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ በአቶ ታዬ ደንደዓ ላይ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ከማሳለፉ ባለፈ በ20 ሺህ ብር ዋስትና ክሳቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉም የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አዟል።
አቶ ታዬ ትናንት ሕዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሹን ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተለቀው ቤተሰቦቻቸውን ሳያገኙ ከማረሚያ ቤቱ በራፍ በጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶቸ ቪሌ ተናግረዋል፡፡
ባለቤታቸው አክለውም ጠዋት ቤተሰብ ሜክሲኮ ምግብ አድርሰዉላቸው ከተመለሱ በኋላ ዛሬ እኩለ ቀን ምሳ ሰዓት ከማቆያው እንዲወጡ ተወስኖ ሰባት ሰዓት አካባቢ መኖርያ ቤታቸዉ መግባታቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡