በካርቱም ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገ ባለበት ሰዓት ሁለቱ ተዋጊዎች በሳዑዲ ለድርድር ይቀመጣሉ
የሱዳን ሁለተኛው ዙር ድርድር በሳዑዲ አረቢያ ሊቀጥል ነው።
ቅዳሜ ዕለት በካርቱም ጎዳናዎች ላይ ታጣቂዎች ከባድ ውጊያ ማካሄዳቸው ተነግሯል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በሳዑዲ አረቢያ ሲቪሎችን ለመጠበቅ የተደረገውን ስምምነት የሚያከብሩ ጥቂት ምልክቶች ማስተዋላችን ገልጸዋል።
ከቀናት በፊት የሱዳን ተፋላሚዎች ንጹሃንን ለመጠበቅና የሰብዓዊ መስመሮችን ለመክፈል በሳዑዲ ተስማምተዋል።
የሀገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሀሙስ ዕለት “የመርሆች መግለጫ” ላይ ከተስማሙ በኋላ ጦርነቱ በካርቱም እና አጎራባች አካባቢዎች እንዲሁም በዳርፉር ግዛት ጂኒና ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከአንድ ወር በፊት የተቀሰቀሰው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል። ከ200 ሽህ በላይ የሚሆኑት ወደ አጎራባች ክልሎች እንዲሰደዱ ያስገደደም ሲሆን፤ 700 ሽህ የሚያህሉ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ መፈናቀላቸው ተነግሯል።
ግጭቱ የውጭ ኃይሎች በመሳብ እና የቀጣናውን መረጋጋት አደጋ ላይ ጥሏልም ተብሏል።
ሳዑዲ አረቢያ ከሁለቱም የጦር አዛዦች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላት ሮይተርስ ዘግቧል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በመቀላቀል በየመን የሁቲ ኃይሎችን በመዋጋት ላይ ነው።