የሱዳን ጦር በሀገሪቱ የተቀሰቀውን ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያ በያዘችው አቋም ዙሪያ አስተያየት ሰጥቷል
የሱዳን ጦር ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በያዘችው አቋም ዙሪያ በዛሬው እለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሱዳን ጦር እና ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤ.ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ 4ኛ ሳምንቱን ይዟል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞም የተለያዩ ሀገራት በጦርነቱ ለሚፋለሙ ሁለቱም ወገኖች ድጋፍን እየሰጡ እንደሆነ ስማቸው የሚጠቀስ ሲሆን፤ ሱዳንም የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን እና ማስተባበያዎችን ስትሰጥ ቆይታለች።
የሱዳን ጦር ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሌተናል ጄነራል ያሲር አልአታ በዛሬው እለት ጦርነቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራያ በጦርነቱ ኢትዮጵያ ለያዘችው አቋም አመስግነዋል።
ሌተናል ጄነራል ያሲር አልአታ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጦርነቱን ተከትሎ ላሳዩት ቁርጠኛ እና ደፋር አቋም እናመሰግናቸዋል ብለዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ከድንበር ጋር ተያየዞ ያለው ችግር በውይይት ብቻ ይፈታል ማለታቸውንም አድንቀዋል።
- ጠ/ሚ ዐቢይ “በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እየሰሩ ነው” ያሉ አካላትን አስጠነቀቁ
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጦርነቱ ውስጥ ከገቡት የሱዳን ጀነራሎች ጋር መወያየታቸውን ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጦርነቱ በተጀመረ የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሱዳን ድንበር አስገብታለች መባሉን ተከትሎ በአረብኛ ቋንቋ ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት "ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ሱዳን ውስጥ አስገብታለች በማለት ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጩ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም "ኢትዮጵያ አሁን ሱዳን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለድንበር ውዝግቡ መጠቀሚያ ልታደርገው አትፈልግም" ማለታቸውም አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ያለው ጉዳይም በውይይት እንደሚፈታ እምነታቸው መሆኑን በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሱዳን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም በአረብኛ ባወጡት መግለጫ፤ ተፋላሚ ወገኖች ውጊያቸውን በማቆም ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።