የሱዳን ጦር፣ የሄሜቲ ጦር ተጨማሪ ኃይል ከዳርፉር ወደ ካርቱም እያንቀሳቀሰ ነው ሲል ከሰሰ
ጦሩ ከዚህ በተጨማሪም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የንግድ ባንኮችን በመዝረፍ ላይ ሲልም ወንጅሏል
ተፋላሚ ኃይሎቹ በሳኡዲ አረቢያ ለመነገገር ስምምነታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል
የሱዳን ጦር፣ በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከዳርፉር ግዛት ተጨማሪ ኃይል ወደ ካርቱም እያንቀሳቀሰ ነው ሲል ከሷል።
ጦሩ ከዚህ በተጨማሪም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የንግድ ባንኮችን በመዝረፍ ላይ ሲልም ወንጅሏል።
በቀረበበት ክስ ዙሪያ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተናገረው የለም።
በሱዳን አጋር በነበሩት ሁለቱ ጀነራሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሶስት ሳምንታትን አስቆጥሯል።
ጦርነቱ ሲጀመር አንስቶ ሁለቱ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ ጫና ቢደረግባቸው በተለያየ ጊዜ የገቧቸውን የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም።
በከፊል ተግባራዊ ሆኖ የነበረው ተኩስ አቁም በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ አማካኝነት የተደረሰው ተኩስ አቁም ስምምነት ነበር።
በሳኡዲ እና በአሜሪካ የተደረሰው ተኩስ ከቁም ለሰባት ቀናት እንዲራዘም የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ማስማማታቸውን ቢገልጹም በድጋሚ ጦርነቱ ቀጥሎ ነበር።
ካርቱም እና ሌሎች ቦታዎች በታንክና መድፍ ድምጾች ሲናወጡ ነበር።
ተፋላሚ ኃይሎቹ በሳኡዲ አረቢያ ለመነጋገር ስምምነታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
በሱዳን ጦርነት ምክንያት በርካቶች ሲገደሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል፤በመሰደድም ላይ ናቸው።