“የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል አለመወሰን የመኖር እና የአለመኖር ጉዳይ ነው” - ኢሰማኮ
በአሁኑ ወቅት በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት እና የፋብሪካ ሰራተኞች ደሞዝ 5 ሊትር ዘይት እንኳን እንደማይገዛ አቶ ካሳሁን ተናግረዋል
ኢሰማኮ የዛሬ አመት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ባደረገው ምክክር ያቀረባቸው ጥያቄዎች እስካሁን ምላሽ አላገኙም
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) “የዝቅተኛ ደምወዝ ወለል አለመወሰን የመኖር እና የአለመኖር ጉዳይ ነው” ብሏል።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የኑሮ ሁኔታ በቋሚ ደምወዝ በሚኖሩ ተቀጣሪ ሰራተኞች ላይ እየፈጠረ ያለው ተጽእኖ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
የኑሮ ውድነቱ ሰራተኛው ከሚያገኝው ገቢ ጋር ሊመጣጠን ባለመቻሉ ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ኑሯቸውን እንዲገፉ አስገድዷል ያለው የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ማስተካካያዎችን እንዲደረጉ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን እና የግብር ቅነሳ እንዲደረግ ኢሰማኮ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በነበረው ውይይት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለሌሎች ተቋማት ጉዳዩን አይተው እንዲያቀርቡላቸው ኃላፊነት ሰጥተው ነበር፡፡
ኢሰማኮ ሀላፊነት ከተሰጣቸው የመንግስት ሚንስቴር መስርያ ቤቶች ጋር በጉዳዩ ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ ከውይይቱ በኋላ በአካል ተገኛኝቶ መክሮ ነበር፡፡
ሆኖም እሳካሁን በጉዳዩ ላይ አንዳች እልባት ባለመሰጠቱ ከ15 ቀናት በፊት ለጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋሜ ጥያቄውን በደብዳቤ ማስገባቱን የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለአል ዐይን አማረኛ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች በእገታ እና ጦርነት ምክንያት ከባድ ህይወት እያሳለፉ መሆናቸውን ኢሰማኮ ገለጸ
የደምወዝ ወለል በኢትዮጵያ አለመኖሩ ቀጣሪዎች ባሻቸው ዋጋ ሰራተኞችን ኢንዲቀጥሩ ፣ የደመወዝ መጠን በአሰሪዎች መልካም ፈቃድ ላይ እንዲወሰን እና ለተመሳሳይ ስራ የተለያየ ክፍያ እንዲፈጸም ስለማድረጉ ኮንፌዴሬሽኑ ይገልጻል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አቶ ካሳሁን እንደሚሉት አሁን ባለው ሁኔታ የኢንዱስትሪ ሰራተኞችን ደምወዝ ከ800 ብር አንስቶ ለዲግሪ ተቀጣሪዎች እስከ 2000 ብር ድረስ በሚሆን ዝቅተኛ ክፍያ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
“ይህ ደሞዎዝ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ የህይወት ጥያቄ ምግብ ፣ መመጠለያ፣ አልባሳት እና የቤት ጥያቄን ሊመልስ ቀርቶ 5 ሊትር ዘይት እንኳን የመግዛት አቅም እንደሌለው የገበያውን ሁኔታ መመልከት በቂ ነው” ሲሉ ያክላሉ፡፡
ሰራተኛው የኑሮ ፍላጎቱን በመጠኑም እንኳን መመለስ ካልቻለ ምርታማነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል የሚሉት አቶ ካሳሁን የዝቅተኛ ደመዎዝ ወለል መወሰን የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡
የኢሰማኮ ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን 95 በመቶ የሚሆኑን የአፍሪካ ሀገራት የዝቅተኛ የደምወዝ ወለል እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
በእኛ ሀገር ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሚሰሩት አልሚዎች በሌሎች ሀገራትም የሚሰሩ በመሆናቸው አሰራሩን ያውቁታል የሚሉት ፕሬዝዳንቱ መነሻውን ለመወሰን በዚህ ልክ ለምን አስቸጋሪ እንደሆነ አላውቅም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ካሳሁን አክለውም ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሚመጡበት “ርካሽ የሰው ሀይል አለ” የሚለው መሳብያ መንገድ ሊቀር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የደመወዝ ወለል የውጭ ባለሀብቶችም ሊገነዘቡት የሚችሉት አለምአቀፋዊ አሰራር ስለሆነ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሻም ተናግረዋል፡፡
ኮንፌደሬሽኑ በጥያቄ መልክ ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል ሌላው የገቢ ግብር ቅነሳን የሚመለከት ነው፡፡
ከ10 ሺ900 ጀምሮ ደመወዝ የሚከፈለው ኢትዮጵያዊ 35 በመቶ ድረስ የገቢ ግብር ይቀነስበታል፡፡ በዚህም ገንዘብ አሁን ካለው የመግዛት አቅም አኳያ 10 ሺህ ብር እና 30 ሺህ ብር የሚከፈለው ደምወዝተኛ እኩል ሊቀረጡ እንደማይገባ በመግለጽ፤ 35 በመቶ የገቢ ግብር የሚጀምርበት ደመወዝ ከፍ እንዲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በ2013 ዓም በሰራው የሰራተኛ ኃይል እና የፍልሰተኞች ዳሰሳ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሰራተኞች የሚከፈለው ያልተጣራ አማካይ ወርሃዊ ደመወዝ 4,127 ብር እንደነበር አስቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ በአለም አቀፉ ሰራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) ዳሰሳ መሰረት፤ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወደ 40.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰራተኞች እንደነበራት ገልጾ፤ከአጠቃላይ የደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች ውስጥ 48 በመቶ የሚሆኑት በመንግስት ዘርፍ ቀሪዎቹ 52 በመቶ ደግሞ በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው እንደሚሰሩ በዳሰሳው ላይ አመላክቷል፡፡
ከሶስት አመታት በኋላ ይህ የሰራተኛ ቁጥር በርካታ ጭማሪ ሊኖረው እንደሚችል ሲጠበቅ ከፍያው ግን እምብዛም ለውጥ ያልታየበት ነው፡፡
የብሔራዊ ባንክ ያደረጋቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተከትሎ በመንግስት ሰራተኛው ላይ የሚፈጠረውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ከ300 በመቶ ድረስ ደምወዝ ለመጨመር ማሰቡ ኮንፈዴሬሽን በመልካም የሚቀበለው ቢሆንም ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ መሆኑ ላይ አይስማማም፡፡
ለመንግስት ሰራተኞች የሚደረገው የደመዎዝ ማሻሻያ የግል ድርጅቶች ተቀጣሪዎችን እና የፋብሪካ ሰራተኞችን እንዲሁም ከመንግስት በጀት ውጪ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን ታሳቢ አለማድረጉንም በቅሬታ መልክ ያነሳል፡፡
የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ሲናገሩ “ገበያው ለሁሉም እኩል ነው በኑሮ ሁኔታው ጫና የሚያስተናግዱት የግሉም የመንግስትም ተቀጣሪ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለአንዱ የደምዎዝ ማስተካከያ ተደርጎ አንዱን ባለበት ቀጥል ብሎ መፍረድ የኑሮ ልዩነቱን ይበልጥ የሚያሰፋው ነው ስለሆነም ዘላቂ መፍትሄው ወጥ የሆነ የደምወዝ ወለልን ማስቀመጥ ነው” ብለዋል፡፡
አቶ ካሳሁን “ነገር ግን በሚቀጥለው አመትም ጥያቄው ይመለሳል ብለን አንጠብቅም፡፡ ምክንያቱም የሰራ እና ክህሎት ሚንስቴር የዝቅተኛ ደመወዝን የሚወስን ቦርድ የሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት በ2017 እቅዱ ውስጥ ነው ያካተተው፡፡
ይህም ማለት ቦርዱ ተቋቁሞ ከእዚያ ደግሞ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን ጥናቶችን ለማጥናት የሚወስደበትን ጊዜ ስታስበው ረጂም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል የሚያሳይ ነው ረሀብ ደግሞ ጊዜ አይሰጥም” ብለዋል፡፡
ከአምስት አመት በፊት የወጣው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ዝቅተኛ ደመወዝን የሚወስን የመንግስት የአሰሪና ሰራተኛ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት “የደመወዝ ቦርድ” እንደሚቋቋም ይደነግጋል።
ይሁን እና ቦርዱ እስከዛሬ ድረስ ሳይቋቋም ቆይቶ የስራ እና ክህሎት ሚንስቴር በ2017 በጀት አመት ቦርዱ በሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ ለመምክር በእቅድ ደረጃ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የውሳኔውን አፈጻጸም ሊያዘገየው እንደሚችል በኢሰማኮ ዘንድ ስጋት አለ፡፡
ኢኮኖሚው መክፈል ከሚችለው በላይ አንጠይቅም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፤ ነገር ግን የውጭ ባለሀብቶችም የሀገር ውስጥ ቀጣሪዎችም የሚያውቁትን በሌሎች ሀገራትም የሚሰራበትን ሰራተኛው የኑሮውን ጫና ሊቋቋምበት የሚችልበት ሚዛናዊ ማሻሻያ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑን ነው ያነሱት፡፡
አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ የደመወዝ ቦርዱ ተቋቁሞ የዝቅተኛ ደመዎዝ ወለል እስኪወሰን አንድአመት ሊፈጅ እንደሚችል ተናግረው፤ መንግስት ከእዚያ በፊት ሰራተኛው የሚገኝበትን ሁኔታ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያጤነው ጥያቄያቸውን ከ15 ቀናት በፊት ለጠቅላይ ሚንስትሩ በድጋሚ በደብዳቤ ማስገባታቸውን ለአል ዐይን አማረኛ አስረድተዋል፡፡