ግብጽ ውስጥ በተነሳ ግጭት ሶሰት እስራኤላውያን ጥቃት ደረሰባቸው
ጉዳቱ የደረሰው የአረብ እስራኤላዊ ጎብኝ ግብጻዊውን የሆቴል ሰራተኛ መስደቡን ተከትሎ በጎብኝዎች እና በሰራተኞቹ መካከል በተፈጠረ ጸብ ነው
የጋዛው ጦርነት ከተከፈተ ከአንድ ቀን በኋላ ሁለት እስራኤላውያን ጎብኝዎች በአሌክሳንድሪያ ከተማ መገደላቸው ይታወሳል
ግብጽ ውስጥ በተነሳ ግጭት ሶሰት እስራኤላውያን ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገለጸ።
ከእስራኤል ጋር በምትዋሰነው ታባ በተባለችው የግብጽ ከተማ በተነሳ ግጭት ሶሰት የአረብ እስራኤላውያን ጎብኝዎች እና ሁለት ግብጻውያን በትናንትናው እለት ጉዳት እንደደረሰባቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ጉዳቱ የደረሰው የአረብ እስራኤላዊ ጎብኝ ግብጻዊውን የሆቴል ሰራተኛ መስደቡን ተከትሎ በጎብኝዎች እና በሰራተኞቹ መካከል በተፈጠረ ጸብ ነው።
ሮይተርስ የግብጹን ለመንግስት ቅርብ የሆነውን አልቀሂራ የተሰኘውን የቴሌቪዥን ቻናል ጠቅሶ እንደዘገበው አንደኛው ግብጻዊ ሰራተኛ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ግጭቱ የተፈጠረው በርካታ ጎብኝዎች ለሆቴል አገልግሎት አንከፍልም ካሉ በኋላ ነው ተብሏል።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በግብጽ በሚኖሩ እስራኤላውያን ላይ አልፎአልፎ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል።
ጦርነቱ ከተከፈተ ከአንድ ቀን በኋላ ሁለት እስራኤላውያን ጎብኝዎች እና ግብጻዊ አስጎብኛቸው በሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ በምትገኘው አሌክሳንድሪያ ከተማ መገደላቸው ይታወሳል። ይህ ጥቃት በእስራኤላውያን ላይ በአስርት አመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ ሆኖ ተመዝግቧል።
እስራኤል በጋዛ በምታደርገው መጠነሰፊ ጥቃት ምክንያት በአረቡ አለም ከፍተኛ ተቃውሞ እያስተናገደች ሲሆን ዜጎቿም የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ።
ግብጽ ከኳታር እና አሜሪካ ጋር በመሆን 40ሺ በላይ ፍልስጤማውያን እንዲገደሉ ምክንያት የሆነው 10 ወራት ያስቆጠረው ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ ጥረት እያደረገች ነው።