የሰራተኞች ቀንን ከማክበር ባለፈ ለሰራተኛው ጥያቄ እና መብት ምን ያህል ትኩረት ይሰጣል?
የሰራተኞች ቀንን ከማክበር ባለፈ ለሰራተኛው ጥያቄ እና መብት ምን ያህል ትኩረት ይሰጣል?
የሰራተኞች ቀን ታሪክ በአሜሪካ የዓለም የሰራተኞች ንቅናቄ ከተጀመረ ከ 125 ዓመት በኋላ ዛሬ ብዙ ሃገራት፣ ምናልባትም ከ80 በላይ የሚሆኑት፣ ዕለቱን ብሔራዊ አድርገው ያከብሩታል፡፡ ዕለቱ የተወሰነውም በ1886 በቺካጎ በተነሳው የሰራተኞች የስምንት ሰዓት ስራ እንዲከበር የተቀጣጠለው አድማ በፖሊሶች በተተኮሰ ጥይት 4 ሰዎች ለህልፈት በመዳረጋቸው እንደሆነም ይነገራል፡፡
በወቅቱ በሰራተኛው በኩል ሰላማዊ ሰልፎች መደረግ የጀመሩት ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ነበር። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኢንዱስትሪው አብዮት ያለማቋረጥ የሚሠሩ አዳዲስ ማሽኖችን በማስገኘቱ የፋብሪካ ባለቤቶች ሠራተኞቻቸው ከዕሁድ በስተቀር በየቀኑ 16 ሰዓት እንዲሠሩ ያደርጓቸው ስለነበር ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስና የካናዳ የንግድና የሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የሠራተኞችን ኑሮ ለማሻሻል ከግንቦት 1 ቀን 1886 ጀምሮ ሠራተኞች በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሠሩ ጥያቄ አቀረበ። ብዙ ቦታ የሚገኙ አሠሪዎች በጥያቄው ባለመስማማታቸው ግንቦት አንድ ቀን ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ፡፡ ይህ ንቅናቄ እያደገ ሄዶ በአሜሪካ የተጀመረው በሌሎችም ሃገራት ድጋፍ ማግኘት ጀመረ፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያም መከበር ከጀመረ 45 ዓመት ሞልቶታል፡፡ ይሁንና በዓሉ ሲከበር ለሰራተኞች ትኩረት በመስጠት አይደለም የሚሉ ድምጾች ይሰማሉ፡፡
ከሰሞኑ ከአል ዐይን ጋር ቆይታ ያደረጉ ሰራተኞች የሰራተኞች ቀን በየዓመቱ እንደሚከበር እንደሚያውቁ በየዓመቱም መልዕክት እንደሚተላለፍ መረጃው እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል በቀን ስራ የሚተዳደረው ስብሐት ምስጋናው በየጊዜው አሰሪና ሰራተኛ የሚፈጥሩት ግጭት መወገድ እንዳለበት ያነሳል፡፡ በተለየ ሁኔታ በዚህ ዓመት የሚከበረው ደግሞ ከኮሮና ጋር ግብ ግብ በተገጠመበት ወቅት ነው የሚለው ስብሐት “ሰራተኛ ስራውን ካላከበረ፣ አሰሪም ሰራተኛውን ካላከበረ ይህንን ወቅት ማለፍ አስቸጋሪ ያደርገዋል”ይላል፡፡ “በዚህ ዓመት ግን ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት ገቢዬ በቂ አይደለም” የሚለው ስብሐት በቀን 100 ብር ብቻ እንደሚያገኝም ያነሳል፤ ይህንንም ለትራንስፖርት ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች እንደሚያውለው ነው የሚገልጸው፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ “ማህበረሰባችን የቤት ኪራይ ላይ ያደረገው እገዛ መልካም ሆኖ ሳለ ምግብ አቅራቢ ቦታዎች በመዘጋታቸው ምክንያት ለምግብ የምናወጣው ወጪ ጨምሯል፡፡ ይህም ህይወትን ዳገት አድርጎብናል” ሲል የሚገልጸው አስተያየት ሰጪያችን፣ ለቤት ኪራይ 1,500 ብር እንደሚከፍል ነግሮናል፡፡
በጽዳት ስራ ላይ የተሰማራቸው ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ሰናይት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተብሎ የተጨመረው የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ትልቅ ተጽዕኖ እንደፈጠረባት ታነሳለች፡፡፡ ለምሳሌ በሀይገር ከተጓዘች 6 ብር ለታክሲ ደግሞ 12 ብር እንደምትከፍልና ይህም ለትራንስፖርት የምታወጣውን የቀን ወጪ 12 ብር ወይም 24 ብር እንዳደረገባት ገልጻለች፡፡ የጽዳት ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ያስታወቀችው ሰናይት ሳኒታይዘር፣ ጓንት እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እንደምትጠቀም አውግታናለች፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ የሚሰሩት ስራና የሚከፈላቸው ደመወዙ እንደማይመጣጠን ነው ያነሱልን፡፡ አሁን ደግሞ ወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ ህይወትን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ያነሳሉ፡፡ በዚህም መሰረት መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት “እኛን ዝቅተኛ ገቢ ያለንን ሰራተኞች እንዲያስቡን እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡ ከላይ አስተያየት ከሰጡን ሰራተኞች በተጨማሪም በርካቶች ከወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከሥራ ልንቀነስ ነው የሚል ስጋት ያነሳሉ፡፡ ይሁንና መንግስት ሰራተኛን ማባረር እንደማይቻል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ ‹‹አሁን ላይ ብዙ ሰራተኞች ስጋት ላይ መሆናቸውንና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰራተኞችን ማባረር አትችሉም ቢልም በዲሲፕሊን ከሆነ ግን ማሰናበት ይችላል ስለሚል እርሱን ሰበብ በማድረግ ብዙ ድርጅቶች ሰራተኞችን ከሥራ እያሰናበቱ ነው›› ይላሉ፡፡
“አንዳንድ ድርጅቶች ሰራተኞችን ከሥራ የማባረር ብቻ ሳይሆን፣ የሰራተኛ ማህበራትን ለማፍረስ፣ የሰራተኛ ማህበራትን ሊቀ መንበሮች፣ ምክትል ሊቀመንበሮች፣ ጸሃፊዎችና ሌሎችም በማባረር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ፍርድ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ሰራተኞች የትም ሄደው አያመለክቱም በሚል ነው”ብለዋል አቶ ካሳሁን፡፡
አንዳንድ ድርጅቶች የሚፈልጓቸውን ሰራተኞች ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ለማሰናበት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ”ቀደም ሲል ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር የምናመለክተው፤ አሁን ግን በወረርሽኙ ምክንያት ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እያቀረብን ነው” ብለዋል፡፡
ሰራተኞች የማህበራት አባል ሆኑም አልሆኑ በደል ሲደርስባቸው ለኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) በአካል ቀርበው ማመልከት እንደሚችሉም ነው አቶ ካሳሁን የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ ከ 2 ነጥብ 5 እስከ 3 ሚሊዮን ሰራተኞች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን በኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) በማህበር አባልነት የታቀፉ 750 ሺ የመንግስትና የግል ሰራተኞች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ እነዚህም በ2,101 ተቋማት ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው፡፡