ሰዋሰው መልቲሚዲያ ከአሜሪካው ዩኒቨርሳል የሙዚቃ ተቋም ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈጸመ
ስምምነቱ ሰዋሰው መልቲሚዲያ የዩኒቨርሳል ሙዚቃ ስራዎችን እንዲጠቀም ያስችለዋል
ኢትዮያዊያን ሙዚቀኞችም ስራዎቻቸውን በቀላሉ ከሀገር ውጪ ላሉ አድማጮቻቸው እንዲያደርሱ ያግዛልም ተብሏል
ሰዋሰው መልቲሚዲያ ከአሜሪካው ዩኒቨርሳል የሙዚቃ ተቋም ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈጸመ።
ዓለም አቀፉ የሙዚቃ አሳታሚ እና አከፋፋይ ድርጅት ዩኒቨርሳል የሙዚቃ ድርጅት መሰረቱን በኢትዮጵያ ካደረገው ሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር የስራ ስምምነት ተፈራርሟል።
ድርጅቱ ለአልዐይን በላከው መግለጫ የስራ ስምምነቱ ሰዋሰው መልቲሚዲያ የዩንቨርሳል ሙዚቃ ስራዎችን ለኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዩኒቨርሳል የሙዚቃ ድርጅት በኩል ለዓለም ለማስተዋወቅ እና አዳዲስ አድማጮችን ለማግኘት ጥሩ እድል እንደሚሆንም ተገልጿል።
ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ዩኒቨርሳል የሙዚቃ ድርጅት በአፍሪካ ያለውን የገበያ እድል የመጠቀም ፍላጎት አለው የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያም የዚሁ አካል ተደርጋ ከሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር ስምምነት ፈጽሟል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት የሙዚቃ አድማጮች ቁጥር እያደገ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን ዓመታዊ የሙዚቃ ስራዎች የ34 በመቶ እድገት አስመዝግበዋል።
ድርጅቱ የሙዚቃ ስራዎችን በዓለም ላይ በማስተዋወቅ፣ ለአድማጭ እና ተመልካቾች በማድረስ የ90 ዓመት ልምድ ያለው ተቋም ነው።
ከኢትዮጵያዊው ሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር የተደረሰው የስራ ስምምነትም ኢትዮጵያያን የሙዚቃ ወዳጆች የዩንቨርሳል ሙዚቃ ድርጅት ስራዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።
ሀገር በቀሉ ሰዋሰው መልቲሚዲያ ጥቅምት 2015 ዓ. ም የተመሰረተ ሲሆን በበይነ መረብ አማካኝነት የሙዚቃ ስራዎችን ለአድማጭ ተመልካቾች በማድረስ ላይ ይገኛል።
ድርጅቱ ከታዋቂዎቹ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና አስቴር አወቀን ጨምሮ ከበርካታ አንጋፋ እና ጀማሪ ሙዚቀኞች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
ድምጻዊያን እንደሰዋሰው አይነት የሙዚቃ ስራዎች ማቅረቢያ መንገዶችን መጠቀም መጀመራቸው የልፋታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ይገለጻል።