የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሊቢያ 3 ለ 1 ተሸንፎ ነው ከውድድሩ ውጭ የሆነው
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአልጀሪያ እየተካሄደ ካለው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ውጭ ሆነ።
ዋልያዎቹ በሊቢያ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፈው ነው ከውድድሩ የተሰናበቱት።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጋቶች ፓኖም ጎል ከመምራት ተነሰቶ የ3 ለ 1 ሽንፈትን ስላስተናገደው ቡድናቸው በሰጡት መግለጫ፥ ሊቢያዎቹ በፍጥነት ያስቆጠሯት የአቻነት ጎል "በተጫዋቾቼ ላይ የተወሰነ ጫና ፈጥሯል" ብለዋል።
- ዋልያዎቹ የግብጽ አቻቸውን 2ለ0 አሸነፉ
- "ግብጾች ወጪ ችለን ካይሮ ተጫወቱ ቢሉንም የክብር ጉዳይ በመሆኑ ውድቅ አድርገነዋል" - የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
ጫና ፈጥሮ የተጫወተው የሊቢያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባዋልም ነው ያሉት።
አሰልጣኙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቡድን መገንባት ላይ ማተኮራቸውንና በአልጀሪያም ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል።
"በተቻለኝ አቅም ቡድኑን ወደፊት ለመውሰድ እየሞከርኩ ነው፤ በአፍሪካ ዋንጫ እና ቻን ውድድር ላይ ተሳትፈናል፤ ይህ ሂደት ነው፤ እየተማረን ነው የምንመጣው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ከአልጀሪያ፣ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ጋር በምድብ 1 ተደልደሎ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን፥ ከሞዛምቢክ ጋር ያደረገውን የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ያለ ግብ ነጥብ መጋራቱ ይታወሳል።
ከአስተናጋጇ ሀገር አልጀሪያ ጋር ባካሄደው ጨዋታ ደግሞ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት መሸነፉ አይዘነጋም።
የትናንት ምሽቱን ጨዋታ አሸንፎ የአልጀሪያን ድል ማድረግ ለመጠባበቅ የተገደደው ቡድን ሽንፈትን አስተናግዶ አንድ ነጥብ ይዞ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል።
ሊቢያም ድል ቢቀናትም ወደ ቀጣዩ ዙር አላለፈችም።
በሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ሊቢያን 3 ለ 2 የረታችው ሞዛምቢክ ትናንት በአልጀሪያ 1 ለ 0 ብትሸነፍም አስተናጋጇን ሀገር ተከትላ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።
ቻን የአፍሪካ ዋንጫ በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት አህጉራዊ ውድድር ነው።