የበርሃ ቀበሮዎቹ ደግሞ ምድቡን በሶስት ነጥብ እየመሩ ነው
7ኛው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ከአስተናጋጇ ሀገር አልጀሪያ የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።
በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ምሽት 4 ስአት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ለዋልያዎቹ ወሳኝ ነው።
የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሞዛምቢክ ያለግብ የተለያየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፥ “በአዕምሮም ሆነ በአካል ለዚህ ጨዋታ ተዘጋጅተናል” ብለዋል።
አልጀሪያ በሜዳው የሚጨወት፣ የኳስ ደረጃቸውም ከፍ ያለ ቢሆንም በሙሉ መተማመን ወደ ሜዳ ለመግባት መዘጋጀታቸውንም ነው ያነሱት።
ከዚሁ ምድቡ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ምሽት 1 ስአት ይጫወታሉ፡፡
ምድቡን አልጀሪያ በሶስት ነጥብ እየመራች ነው፤ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ይከተላሉ።
የመጨረሻው የምድብ ጨዋታ የፊታችን ቅዳሜ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ከሊቢያ ምሽት 1 ስአት፤ አልጀሪያ ከሞዛምቢክ ምሽት 4 ስአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኮቲዲቯር፤ ሴኔጋል ከኡጋንዳ የሚጫወቱ ይሆናል።
በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ባለፈው ሳምንት አርብ ነው የተጀመረው።
በአራት የአልጀሪያ ከተሞች እየተካሄደ ባለው ውድድር ሞሮኮ ከአስተናጋጇ ሀገር በገባችበት የፖለቲካ ሰጣ ገባ ሳትሳተፍ ቀርታለች።
የአፍሪካ እግርኳስ ፌደሬሽን ካፍም በመክፈቻው ጨዋታ የተላለፉ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ጉዳዮች እመረምራለሁ ማለቱ ይታወሳል።