ሸራተን ሆቴል ከድምጻዊ ሬማ ጋር ይዞት የነበረውን የአዲስ ዓመት ዋዜማ ኮንሰርት ሰረዘ
በምትኩም ከሌሎች የአፍሮ ቢት ሙዚቀኞች ጋር የአዲስ ዓመት ዋዜማ ኮንሰርት ማዘጋጀቱን አስታውቋል
የኮንሰርቱ ስፖንሰር የነበረው ኮካ ኮላ እና ድምጻዊ ኩኩ ሰብስቤ ከዝግጅቱ ራሳችንን አግልለናል ብለዋል
ሸራተን ሆቴል ከድምጻዊ ሬማ ጋር ይዞት የነበረውን የአዲስ ዓመት ዋዜማ ኮንሰርትን ሰረዘ፡፡
የ2016 አዲስ ዓመትን አስመልክቶ በሸራተን አዲስ ሆቴል የሙዚቃ ድግስ መዘጋጀቱን የሚገልጹ ማስታወቂያዎች ሲተላለፉ ሰንብተዋል፡፡
በዚህ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ድምጻዊያን የማስታወቂያው አንድ አካል የነበሩ ሲሆን ናይጀሪያዊው ዲቫይን ኢኩቦር ወይም በቅጽል ስሙ ሪማ በመባል የሚታወቀው ድምጻዊ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ድምጻዊያን ጋር በመድረኩ ላይ እንደሚዘፍኑ ተገልጾም ነበር፡፡
ይሁንና ድምጻዊ ሬማ ከክርስትና ሀይማኖት ጋር በተያያዘ ያልተገባ ነገር አድርጓል በሚል በአዲስ ዓመት ዋዜማ የሙዚቃ ድግሱ ላይ መሳተፍ የለበትም በሚል በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ቅስቀሳ ሲደረግ ሰንብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም በይፋ የቤተ ክርስቲያን በዓላት ሲደርሱ ከሥርዓቷ እና ከአስተምሮዋ ውጪ በሆነ መልኩ የተለያዩ አካላት "የዳንንኪራ ጥሪ በማዘጋጀት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አግባብነት የሌለው" መሆኑን እና ምዕመናንም ከዚህ እንቅስቃሴ እራሳቸውን ሊያርቁ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፋለች፡፡
ይህን ተከትሎም በዚህ የሙዚቃ ድግስ ላይ ስራዎቿን ለታዳሚያን እንደምታቀርብ የገለጸችው ድምጻዊ ኩኩ ሰብስቤ የቤተ ክርስቲያኗን ጥሪ መቀበሏን እና በአዲስ ዓመት ዋዜማ በሸራተን ሆቴል የሙዚቃ ስራዎቿን እንደማታቀርብ ገልጻለች፡፡
ነየዚህ የሙዚቃ ድግስ አንዱ አጋር የሆነው ኮካኮላ በበኩሉ የሸራተን የአዲስ አመት ዋዜማ ኮንሰርት ስፖንሰርነቱን መሰረዙን ገልጿል፡፡
ድርጅቱ በመግለጫው “በአዲሱ ዓመት ዋዜማ በሸራተን አዲስ ሊከናወን የተሰናዳውን የሙዚቃ ድግስ ድርጅታችን ኮካ-ኮላ ቤቭሬጅስ አፍሪካ~ኢትዮጵያ ስፖንሰር አጋር የነበረ መሆኑ ይታወሳል፤ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያቶች የስፓንሰርሺፕ አጋርነታችንን የሰረዝን መሆኑንና የፕሮግራሙ አጋር አለመሆናችንን እናሳውቃለን“ ብሏል፡፡
የአዲስ ዓመት ዋዜማ የሙዚቃ ድግስ ያዘጋጀው ሸራተን ሆቴል በበኩሉ ከናይጀሪያዊው ሬማ ጋር የተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት መሰረዙን ገልጾ በምትኩ የአፍሪካ ስልተ ምት ሙዚቀኞችን እና ታዋቂ ዲጄዎች በዕለቱ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ብሏል፡፡
የድምጻዊ ሬማን መገኘት በማስመልከት ኮንሰርቱን ለመታደም ትኬት የገዙ ሰዎች ገንዘባቸው እንዲመለስ ከፈለጉ ገንዘባቸውን ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንም ነው ሆቴሉ ያስታወቀው።
በቀጣይ በዚህ ኮንሰርት ላይ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ድምጻዊያንን ስም ይፋ እናደርጋለንም ብሏል፡፡