ፖለቲካ
ደቡብ አፍሪካውያን ብሪታኒያ የንግስና ዘውድ ላይ የተቀመጡ አልማዞችን እንድትመልስ ጠየቁ
አልማዙ ከክፈለ ዘመን በፊት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን ለንጉሳዊ አገዛዙ "መበርከቱ" ተነግሯል
ቅኝ ተገዢ ሀገራት ከነጻነት በተጨማሪ የተዘረፉ ሀብቶቻችን ማስመለስ አለባቸው ተብሏል
ደቡብ አፍሪካውያን ብሪታንያ በነገው እለት ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ ንግሳቸውን በሚያከብሩበት በትር ላይ የተቀመጠውን "የአፍሪካ ኮከብ" በመባል የሚታወቀውን የዓለም ትልቁን አልማዝ እንድትመልስ እየጠየቁ ነው።
530 ካራት አልማዝ በደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ1905 የተገኘ ሲሆን፤ በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረው በሀገሪቱ መንግስት ለእንግሊዝ ንጉሳዊ አገዛዝ መበርከቱ ተነግሯል።
በቅኝ ግዛት ዘመን ስለተዘረፉት የጥበብ ስራዎች እና ቅርሶች ዓለም አቀፍ ውይይት እየተደረገ ባለበት ወቅት አንዳንድ ደቡብ አፍሪካውያን አልማዙ እንዲመለስ እየጠየቁ ነው።
"አልማዙ ወደ ደቡብ አፍሪካ መመለስ አለበት። የኩራታችን፣ የቅርሳችን እና የባህላችን ምልክት መሆን አለበት" በማለት በጆሃንስበርግ የህግ ባለሙያና ተሟጋች ሙትሲ ካማንጋ ህዝባዊ ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው።
እስካሁን ስምንት ሽህ የሚጠጉ ሰዎች መፈረማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"እኔ እንደማስበው በአጠቃላይ የአፍሪካ ህዝቦች ከቅኝ ግዛት መውጣታቸው ሰዎች ነጻነት እንዲኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከኛ የተዘረፈውን መመለስ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ጀምረዋል" ብለዋል።