ደቡብ ኮሪያ የሰባት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን አዋጀች
ከታይላንድ ወደ ደቡብ ኮሪያ በመብረር ላይ የነበረ የመንገደኞች አውሮፕላን ተከስክሶ የ179 መንገደኞች ህይወት ማለፉ ይታወሳል
በጊዜያዊ ፕሬዝዳንት የምትመራው ደቡብ ኮሪያ ከባድ ሐዘን ላይ ትገኛለች
ደቡብ ኮሪያ የሰባት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን አዋጀች
የጀጁ አየር መንገድ ንብረት የሆነ የበረራ ቁጥሩ 7C2216 የተሰኘ አውሮፕላን በደቡብ ኮሪያ ተከስክሷል።
ቦይንግ 737-800 ስያሜ ያለው አውሮፕላን በዛሬው ዕለት የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ 181 መንገደኞችን ከታይላንድ ባንኮጭ ጭኖ እየበረረ እያለ በደቡብ ኮሪያዋ ሙዓን ኤርፖርት ለማረፍ ሲሞክር ተከስክሷል።
የደቡብ ኮሪያ አደጋ መቆጣጠር ተቋም እንዳለው 179 ሰዎች መንገደኞች መሞታቸው ሲረጋገጥ ሁለት ሰዎች ደግሞ በህይወት ተርፈዋል።
የደቡብ ኮሪያ ዜና ወኪል የሆነው ዮናፕ እንደዘገበው ከሆነ የወቅቱ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ቾይ ሳንግ ሞክ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን ቀናት አውጀዋል፡፡
ጀጁ አየር መንገድ ለተፈጠረው አደጋ የሟች ቤተሰቦችን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ቦይንግ ለሟቾች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
በዛሬው ዕለት ብቻ የሞዓይ ኤርፖርት አደጋን ጨምሮ ሶስት አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን በካናዳ አየር መንገድ እና በሆላንዱ ኬኤልኤም አየር መንገዶች ላይ አደጋ አጋጥሟል፡፡
ከደቡብ ኮሪያው ውጭ ያሉ ሁለት አየር መንገዶች ላይ ያጋጠሙት አደጋዎች ቀላል እና የሰው ህይወት አላለፈባቸውም፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት የአዛርባጂያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን ከባኩ ወደ ሞስኮ በመብረር ላይ እያለ መከስከሱ ይታወሳል።
በአደጋው 38 ሰዎች ሞተዋል የተባለ ሲሆን አውሮፕላኑ በሩሲያ ሚሳኤል ተመቶ እንደወደቀ ዘግይተው በወጡ ሪፖርቶች ላይ ተጠቅሷል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን የአዛርባጂያ ህዝብ እና መንግስትን ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን በወቅቱ ጦራቸው ከዩክሬን የተተኮሱ ድሮኖችን በማምከን ላይ ነበሩም ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራዎች በመደረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ፑቲን ተጠያቂነት እንደሚኖርም ተናግረዋል።
የአዛርባጂያ ፕሬዝዳንት አሊየቭ በበኩላቸው የሩሲያ መንግስት አውሮፕላኑ እንዲመታ ያደረጉ አካላት ተገቢው ቅጣት እንዲጣልና ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡