ሰሜን ኮሪያ ጂፒኤስ በመጥለፍ የአውሮፕላንና መርከቦችን ጉዞ ማወኳን ደቡብ ኮሪያ ገለጸች
የአቅጣጫ መጠቆሚያ ስርአቱ በምዕራባዊ የድንበር አካባቢዎች ላይ ትናንትና ዛሬ መጠለፉን ነው ሴኡል ያስታወቀችው
በአመት ከ56 ሚሊየን በላይ ሰዎች የሚያጓጉዘው የደቡብ ኮሪያ ዋነኛው አውሮፕላን ማረፊያ ከሰሜን ኮሪያ ከ100 ኪሎሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ይገኛል
ሰሜን ኮሪያ ከሳተላይቶች መረጃ በመሰብሰብ አቅጣጫ የሚጠቁመውን የጂፒኤስ ስርአት መጥለፏን ደቡብ ኮሪያ ገለጸች።
ፒዮንግያንግ ትናንት እና ዛሬ የጂፒኤስ ስርአት ላይ ለመጥለፍ ባደረገችው ሙከራ በደርዘን የሚቆጠሩ አውሮፕላኖች እና መርከቦች ጉዞ መታወኩንም ነው የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
የአቅጣጫ እና ሌሎች መረጃ ማቀበያ የጂፒኤስ ስርአቱ ኬሶንግ በተባለችው ከተማ ስለመጠለፉ የገለጸችው ሴኡል፥ መርከቦች እና አውሮፕላኖች በምዕራባዊ ሰሜን ኮሪያ አቅራቢያ ጉዞ እንዳያደርጉ አሳስባለች።
ሰሜን ኮሪያ በምን መንገድ ጂፒኤስ እንደጠለፈች እና ምን ያህል አውሮፕላኖች እና መርከቦች ጉዟቸው እንደተስተጓጎለ ግን አላብራራችም።
“ሰሜን ኮሪያ ጸብ አጫሪ ከሆነው የጂፒኤስ ጠለፋ ልትታቀብ ይገባል፤ በዚህ ምክንያት ለሚደርስ ጉዳትም ሙሉ ሃላፊነቱን እንደምትወስድ ልናሳስብ እንወዳለን” ብሏል የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።
በፒዮንግያንግ የቆሻሻ ፊኛዎች ምክንያት በረራው ተስተጓጉሎ የነበረው የደቡብ ኮሪያ ዋነኛው አውሮፕላን ማረፊያ የጂፒኤስ ስርአት ጠለፋው ሰለባ ሊሆን እንደሚችል አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በአመት ከ56 ሚሊየን በላይ ሰዎችና ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ቶን በላይ ጭነት የሚያጓጉዘው የኢንቾይን አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሰሜን ኮሪያ ከ100 ኪሎሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ይገኛል።
ፒዮንግያንግ ከወራት በፊት በቆሻሻዎች የተሞሉ ፊኛዎችን 12 ጊዜ በዚህ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በመጣሏ ምክንያት ለ265 ደቂቃዎች በረራዎች መዘግየታቸው ተገልጾ ነበር።
ደቡብ ኮሪያን በህገመንግስቷ ጭምር “ጠላት” አድርጋ የፈረጀችው ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል እና ኒዩክሌር ፕሮግራሟን አጠናክራ በቅርቡም አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።
ይህን ሙከራዋን ተከትሎ አሜሪካ ከአጋሮቿ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር የሶስትዮሽ የአየር ልምምድ ማድረጓ አይዘነጋም።
ፒዮንግያንግ ለዚህ ምላሽም አሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ባካሄድችበት እለት (ማክሰኞ) በጥቂቱ ሰባት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የሁለቱን ኮሪያዎች መሪዎች ከጦርነት ነጻ በሆነው ቀጠና (ዲኤምዜድ) እጃቸውን ያጨባበጡት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም መመረጣቸው የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት ሊያረግበው እንደሚችል ተገምቷል።