ደቡብ ኮሪያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት የተለያዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ ከሰሜን ኮሪያ ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ገለጸች
የቤተሰቦች መገናኘት የቆመው ከፈረንጆቹ 2019 ወዲህ ነው
ለመገናኘት ካመለከቱት ሰዎች 70 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉን የደቡብ ኮሪያ ዩኒፊኬሽን ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል
አዲሱ የደቡብ ኮሪያ መንግስት በ1950ዎቹ በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት ወቅት የተለያዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ ለማድረግ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመነጋገር ማቀዱን ገልጿል።
በደቡብ እና ሰሜን ኮሪያ መካከል በኑክሌር የጦር መሳሪያ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ የቆየ አለመግባባት አለ።
የቤተሰቦች መቀላቀል ጉዳይ እጅግ ሰብአዊና ሰሜታዊ የሚያደርግ ጉዳይ ነው።
ነገርግን ሰሜን ኮሪያ የቤተሰቦችን መገናኘት ጉዳይ ከደቡብ ኮሪያ ጋር እንደመደራደሪያ ስለምትቆጥረው፣ሰሜን ኮሪያ የደቡብ ኮሪያን መንግስት እቅድ ላትቀበለው ትችላለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የኑክሌር አቅሟን በማሳደግ ላይ ያለችው ሰሜን ኮሪያ፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ከአሜሪካ የቀረበላትን በኑክሌር ጉዳይ ውይይት በንቀት አልፋዋለች።
"ደቡብ እና ሰሜን የሚያመውን እውነታ መጋፈጥ አለባቸው፤የተለያዩ ቤተሰቦች የሚለው ቃል ከመጥፋቱ በፊት ችግሩን መፍታት አለብን" ሲሉ የውህደት ሚኒስትር ክዎን ዮንገዜ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው የሁለቱ ኮሪያዎች በአካል ተገናኝተው ልባዊ እንደሚያደርጉ ተስፋ አለኝ ብለዋል።
የሁለቱ ኮሪያዎች የቤተሰብ መገናኘቱ የቆመው በፈረንጆቹ 2019 አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሟን እንድታቆምና በምትኩ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥቅም እንድታገኝ ያደረገችው ወይይት ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።
አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ያለቅድመ ሁኔታ ወደ ኑክሌር ውይይት እንድትመጣ ብትጠይቅም፣ ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላትን ጸብ አጫሪ ፖሊሲ መተው አለባት ስትል ቆይታለች።
ከበርካታ አስርት አመታት በኃላ የሚፈላለጉት ቤተሰቦች በህይወት ይኖሩ ይሆን እያሉ ይጨነቃሉ።
እንደ ዩኒፊኬሽን ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከ133ሺ በላይ ሰዎች በሰሜን ኮሪያ ካሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ያመለከቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ሳይገናኙ ህይወታቸው አልፏል።