ሰሜን ኮሪያ፤ የአሜሪካን "በቻይና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት" በጽኑ አወገዘች
ፒዮንግያንግ የፔሎሲን የታይዋን ጉብኝት በመቃወም ለመጀመሪያ ጊዜ አስተያየት ሰጥታለች
ቻይና ሉዓላዊና ግዛታዊ አንድነቷን ለመጠበቅ ለያዘችው አቋም ሙሉ ድጋፍ አለኝም ብላለች
ሰሜን ኮሪያ፤ አሜሪካ በቻይና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ወቀሰች።
ወቀሳው የአፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲን የታይዋን ጉብኝት አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ ነው።ፔሎሲ ለይፋዊ ጉብኝት ትናንት ማክሰኞ ጠዋት ታይዋን ገብተዋል።
አፈ ጉባኤዋከ25 ዓመታት በኋላ ታይዋንን የጎበኙ የመጀመሪያዋ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ናቸው።ይህም ታይዋንን አንድ የሉዓላዊ ግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥረውን ቻይናን ክፉኛ አስቆጥቷል።
በሉዓላዊና ግዛታዊ አንድነቴ ላይ የተሰነዘረና በቀጠናው ውጥረትን የሚያነግስ ጸብ አጫሪ ጥቃት ስትልም ነው የአሜሪካን ድርጊት የኮነነችው።
ሰሜን ኮሪያም ከቻይና ጎን በመቆም ድርጊቱን አውግዛለች። በአሜሪካ እና በምዕራባዊ አጋሮቿ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንድትገለል የሚያደርግ ጫና የበረታባት ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር የቀረበ ወዳጅነት አላት።
ያለ አንዳች ሃፍረት የተደረገ ነው በሚል የአሜሪካን ድርጊት የኮነነው የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በቀጣናው ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ውጥረት ዋና ምክንያት ይህን መሰሉ የዋሽንግተን ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ታይዋን ከቻይና ልትነጠል የማትችል አንድ አካሏ እንደሆነችና እሷን የሚመለከት የትኛውም ዐይነት ጉዳይ የቻይና የውስጥ ጉዳይ እንደሆነም ነው መግለጫው የሚያትተው።ቻይናን ጨምሮ የትኛውም ሃገር በሉዓላዊነቱ ላይ ለሚቃጣ እንዲህ ዐይነት ጥቃት ለሚሰጣቸው የአጸፋ ምላሾች ያለውን ድጋፍም ገልጿል ሚኒስቴሩ።
በታይዋን ጉዳይ የሚደረጉ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን በማውገዝም የቻይና መንግስት ሉዓላዊና ግዛታዊ አንድነቱን ለመጠበቅ ለያዘው አቋም ሙሉ ድጋፍ እንዳለውም አስታውቋል።