ሩሲያ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾችን ከሰሜን ኮሪያ እየገዛች ነው ተባለ
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት እንዳለው ሩሲያ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት የጦር መሳሪያ ግብዓት እጥረት ገጥሟታል
ሩሲያ በበኩሏ ኢኮኖሚዋ በመሻሻል ላይ መሆኑን አስታውቃለች
ሩሲያ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾችን ከሰሜን ኮሪያ እየገዛች ነው ተባለ፡፡
ኒዮርክ ታይምስ የአሜሪካ የስለላ ተቋም መረጃን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ምክንያት የጦር መሳሪያ እጥረት አጋጥሟታል፡፡
ሩሲያ የየከባድ ጦር መሳሪያ ተተኳሽ እጥረት ያጋጠማት በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት በተጣለባት ማዕቀብ እንደሆነ የጠቀሰው ዘገባው እጥረቱን ለማስታገስ ስትልም ከሰሜን ኮሪያ በመግዛት ላይ መሆኗንም ጠቅሷል፡፡
አሁን ላይ ሩሲያ ሮኬቶች እና ሌሎች የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት ተገዳለች ያለው ዘገባው ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር የጦር መሳሪያውም የበለጠ እያጠራት እንደሚሄድ አመላክቷል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሩሲያ ኢራን ሰራሽ ድሮኖችን ከቴህራን መግዛቷን የገለጸው ዘገባው ሩሲያ በአሜሪካ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሀገራት ጋር ግንኙነቷን እያጠበቀች መጥታለችም ብሏል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መጀመር ዋነኛዋ ተጠያቂ አሜሪካ እንደሆነች ከዚህ በፊት ተናግረው ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ለተጠቃለሉ ዶምባስ እና ሉሃንስክ ግዛቶች ሉዓላዊነት ቀድመው እውቅና ከሰጡ ሀገራት መካከል ሰሜን ኮሪያ አንዷ ስትሆን ሶሪያ ደግሞ ሁለተኛዋ ሀገር ናት፡፡
ሩሲያ በበኩሏ በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች ቢጣሉብኝም ማዕቀቦቹ በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሱት ተጽዕኖ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
የሞስኮ መገበያያ የሆነው ሩብል ከአሜሪካው ዶላር ጋር ሲነጻጸር ከዚህ በፊት ከነበረው ልዩነት መቀነሱን እና የሩሲያ የወጪ ንግድም ጉድለት አለማሳየቱ ተገልጿል፡፡
የፊንላንዱ የምሁራን ስብስብ ተቋም ባወጣው ጥናት ምዕራባዊያን በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ጥቂት ጉዳት ብቻ ማድረሱን ጠቅሶ ሩሲያ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 136 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን አስታውቋል፡፡