በቁጥጥር ስር የዋሉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት በወንጀል መርማሪዎች እየተጠየቁ ነው
ዩን በስልጣን ላይ እያሉ የታሰሩ የመጀመሪያው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ሆነዋል
ዩን ህገ ወጥ ያሉት ምርመራ እንዲካሄድባቸው የተስማሙት "ደም መፋሰስን" ለማስቀረት ነው ብለዋል
በቁጥጥር ስር የዋሉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት በወንጀል በመርማሪዎች እየተጠየቁ ነው።
ከስልጣን የታገዱት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዘደንት ዩን ሱክ የኦል በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ አመጽ ለማስነሳት አሲረዋል ባሏቸው ባለስልጣናት እየተጠየቁ እና እየተመረመሩ ይገኛሉ።
ዩን ህገ ወጥ ያሉት ምርመራ እንዲካሄድባቸው የተስማሙት "ደም መፋሰስን" ለማስቀረት ነው ብለዋል። በሀገሪቱ በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝደንት ሲታሰር የመጀመሪያ ሲሆን ጠንካራ ዲሞክራሲ ያላትን እስያዊት ግራመጋባት ውስጥ ከቷታል።
ዩን ባወጁት ለአጭር ጊዜ በቆየ ወታደራዊ አዋጅ ምክንያት በፓርላማ ከስልጣን ከታገዱበት ከባለፈው ታህሳስ 3፣2024 ጀምሮ ቀደም ሲል የተካሄዱ የመያዝ ሙከራዎችን ባከሸፉ ጥቂት ወታደሮች እየተጠበቁ በተራራ ስር ባለው ቤታቸው መሽገው ቆይተዋል።
እምቢ ባዩ ዩን በዛሬው እለት ጠዋት እሳቸውን ለመያዝ 3000 ሺ ፖሊሶች ወደ መኖሪያ ቤታቸው መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ግጭት ለማስቀረት ሲሉ እጃቸውን መስጠታቸው ተናግረዋል።
"ምንም እንኳን ህገ ወጥ ምርመራ ቢሆንም ደም መፋሰስን ለማስቀረት ስል ለሲአይኦ መልስ ለመስጠት ወስኛለሁ" ሲሉ ዩን ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ቆየት ብሎ ዩን በእጀባ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው እና በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የሙስና ምርመራ ወደሚያደርገው ቢሮ (ሲአይኦ) ተወስደዋል። ባለስልጣናት አሁን ላይ ዩንን ለመጠየቅ 48 ሰአታት ያላቸው ሲሆን እስከ 20 ቀናት ለማሰር ትዕዛዝ ሊጠይቁ ወይም ሊለቋቸው ይችላሉ ተብሏል።
የመያዣ ትዕዛዙ ትክክለኛ ስልጣን በሌለው ፍርድ ቤት በመውጣቱ ህገወጥ ነው ያሉት የዩን ጠበቃ የተቋቋመው ቡድንም ዩንን የመመርመር ኃላፊነት የለውም ብለዋል።
የዩን ወታደራዊ አዋጅ ደቡብ ኮሪያውያንን ከማስደንገጥ አልፎ በእስያ በኢኮኖሚዋ አራተኛ ደረጃ ላይ ያለችውን እንዲሁም የዋሽንግተን ቁልፍ የጸጥታ አጋር የሆነችውን ደቡብ ኮሪያን ወደአልተጠበቀ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ አስገብቷታል።
የፓርላማ አባለት ዩንን ከስልጣን ያነሷቸው ታህሳስ 14፣2024 ነው።
የሀገሪቱ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት በዩን ላይ የተጣለውን እገዳ ለማጽናት እና በቋሚነት ከስልጣን ለማንሳት ወይም ፕሬዝደንታዊ ስልጣናቸውን ለመመለስ እየመረመረ ይገኛል።
የዩን ከስልጣን መነሳት እና እስር ደቡብ ኮሪያውያንን በተቃውሞ እና በድጋፍ በሁለት ጎራ አስልፏል።