አስከፊ የአውሮፕላን አደጋ የተከሰተባት ደቡብ ኮሪያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ከስልጣናቸው ሊለቁ ነው
ሚኒስትሩ ከሳምንት በፊት ለደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሀላፊነት ለመውሰድ ነው ከስልጣናቸው የሚለቁት
በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የአቭየሽን ደህንነት ስርአቶች ላይ ፍተሻ እንዲደረግ በመንግስት መታዘዙ ይታወሳል
የደቡብ ኮሪያ የትራንስፖርት ሚኒስትር በጄጁ አየር መንገድ አውሮፕላን ለደረሰው አደጋ ኃላፊነቱን ለመውሰድ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ማሰባቸውን አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ፓርክ ሳንግ ዎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ለዚህ አደጋ ከባድ ኃላፊነት ይሰማኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ የአደጋውን መንስኤ አጠቃላይ የምርመራ ውጤት እና አሁን ያለውን ችግር ከፈቱ በኋላ ስልጣን የሚለቁበትን ትክክለኛ ጊዜ አሳውቃለሁ ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ተቋማቸው 179 ሰዎች ለሞቱበት አሰቃቂ አደጋ አስተዋፅዖ አድርገዋል ያላቸውን የኤርፖርት ማረፊያ ስርዓቶችን ደህንነት በፍጥነት እንደሚያሻሽል አስታውቀዋል።
የአየር ደኅንነት ባለሙያዎች በአየር ማረፊያ አቅራቢያዎች የሚገኙ የራዳር አንቴናዎች እና ግንቦች ከማኮብኮቢያዎች አቅራቢያ መተከላቸው ሌላ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
በዚህም በፍጥነት በመላ ሀገሪቱ የመሰረተ ልማት መሻሻያዎች ፍተሻ እንዲደረግ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
የትራንስፖርት ምክትል ሚኒስትር ጆ ጆንግ በበኩላቸው በመላ ሀገሪቱ የአቭየሽን ደህንነት ስርአቶች እና መሰረተ ልማቶች ፍተሻ እንዲደረግ የጄጁ አውሮፕላን አደጋ ማንቂያ ደውል ነው ብለዋል፡፡
ፖሊስ ባለፈው ሳምንት በአደጋው ላይ ባደረገው ምርመራ ጄጁ አአየር መንገደ እነሰ እና የሙን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ድንገተኛ አሰሳ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም ሁለት የኮሪያ አደጋ መርማሪዎች በአደጋው ወቅት የተጎዳውን የበረራ መረጃ መቅጃ ለመገምገም እና ለመተንተን ከአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ጋር ሰኞ ወደ አሜሪካ አቅንተዋል።
ፋይሎችን ከበረራ ዳታ መቅጃ ለማውጣት ሶስት ቀናትን የሚወስድ ሲሆን አደጋው ሞተሩ ላይ ባጋጠመው አደጋ ከማረፍያ ሜዳው ውጭ መንሸራተቱን ለማረጋገጥ ነው መርማሪዎቹ ወደ አሜሪካ ያቀኑት