የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ፕሬዝደንቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ መቅረቱ ተገለጸ
በዩን ለህግ ተገዥ አለመሆን ያዘነው ሲአይኦ ለባለስልጣናቱ ደህንነት ሲል ዩንን በቁጥጥር ስር የማዋል ጥረቱን አቁሟል
ሲአይኦ አሁን በቀጣይ ምን እርምጃዎችን እንደሚወስድ ሁኔታዎችን እየገመገመ እንደሚገኝ ገልጿል
የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ፕሬዝደንቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያደረጉት ጥረት በጸጥታ አካላት ፍጥጫ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱ ተገለጸ።
ባለስልጣናቱ ወታደራዊ አዋጅ በማወጃቸው ምክንያት የታገዱትን ፕሬዝደንት ዩን ሱክን በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር ለማዋል ያረጉት ጥረት ከፕሬዝደንታዊ የጥበቃ አባላት ጋር በተፈጠረ ፍጥጫ ሳይሳካ ቀርቷል።
ዩን እሳቸውን በቁጥጥር ስር ለማድረግ የሚደረግን ጥረት እንሚያስቆሙ ሲዝቱ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በማለዳ በፕሬዝደንታዊ መኖሪያ ደጃፍ ተሰብስበው ተቃውሞ ማሰማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዩን ያወጁቱን ለአጭር ጊዜ የቆየውን ወታደራዊ ህግ እየመረመረ ካለው በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የሙስና ምርመራ ከሚያደርገው ተቋም(ሲአይኦ) የመጡ ባለስልጣናት ገና ሳይነጋ ነበር ቤተመንግስቱ መግቢያ በር ላይ የደረሱት።
ወደ ቤተመንግስቱ ከገቡ በኋላ የሲአይኦ ባለስልጣናት እና አብረዋቸው የነበሩ ፖሊሶች በቤተመንግስቱ የጸጥታ አገልግሎት እንዲሁም በወታደሮች መከበባቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የመከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮቹ በቤተመንግስቱ የጸጥታ አገልግሎት ስር ናቸው ብሏል።
በዩን ለህግ ተገዥ አለመሆን ያዘነው ሲአይኦ ለባለስልጣናቱ ደህንነት ሲል ዩንን በቁጥጥር ስር የማዋል ጥረቱን አቁሟል።
"አሁን እየተካሄደ ባለው ፍጥጫ ምክንያት የእስር ማዘዣውን ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው"ብሏል ሲአይኦ ባወጣው መግለጫ።
የዩን ጠበቃ ባለፈው አርብ እለት ባወጣው መግለጫ ዩንን ለማሰር የወጣው ትዕዛዝ ህጋዊ አለመሆኑን እና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ መግለጹ ይታወሳል።
ፍርድ ቤት በዩን ላይ የቀረበውን የእስር ማዘዣ ያጸደቀው ዩን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለጥያቄ ተፈልገው ባለመቅረባቸው ነበር።
ሲአይኦ አሁን በቀጣይ ምን እርምጃዎችን እንደሚወስድ ሁኔታዎችን እየገመገመ እንደሚገኝ ገልጿል።