ደቡብ ሱዳን ባህር አል ጀበል በተሰኘው ወንዝ ላይ ግድቦችን ልትገነባ መሆኑን አስታወቀች
ባህር አል ጀበል ወንዝ ከዩጋንዳ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚፈስ የናይል ገባር ወንዝ ነው
ግድቡ የሚገነባበት ቦታ ከደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ 403 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው
ደቡብ ሱዳን ባህር አል ጀበል በተሰኘው ወንዝ ላይ ግድቦችን ልትገነባ መሆኑን አስታውቃለች።
ከናይል ወንዝ ተፋሰስ አባል አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ደቡብ ሱዳን ሶስት ገድቦችን ለመገንባት ማቀዷን ገልጻለች።
የደቡብ ሱዳን ውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ማናዋ ፒተር ጋትኩዝ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት አገራቸው ያለባትን የኤሌክትሪክ ችግር ለመፍታት ግድቦችን ለመገንባት ማቀዷን ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ አገራቸው ከዋና መቀመጫ ከሆነችው ከጁባ ከተማ 403 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ካለው ባህር አል ጀበል ወንዝ ላይ ሀይል ለማመንጨት ፕሮጀክት ቀርጻለች።
አገሪቱ ከነበረችበት ጦርነት አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ወደ ሀይል ልማት ማዞሯን የገለጸች ሲሆን የዚህ ግድብ ስራ ዲዛይን እና የአዋጭነት ጥናቱ መጠናቀቁ ተገልጿል።
ለዚህ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ቦታ የማፈላለጉ ስራ መጠናቀቁን የገለጹት ሚኒስትሩ በቀጣይ ገንዘቡ እንደተገኘ የግድቡ ግንባታ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
ባህር አል ጀበል የተሰኘው ወንዝ መነሻው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ሲሆን በዩጋንዳ ከዚያም በደቡብ ሱዳን አድርጎ ወደ ናይል ወንዝ የሚፈስ ወንዝ ነው።
ከ11 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ደቡብ ሱዳን 93 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ሀይል የሚያገኘው ከነዳጅ ሲሆን 7 በመቶ ደቡብ ሱዳናዊያን ደግሞ ከውሃ የተገኘ ኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ናቸው።
ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የምስራቃዊ ናይል ተፋሰስ አገራት ጉባኤ ከአንድ ወር በፊት ባካሄዱት ጉባኤ የአካባቢውን አገራት በጋራ የሚያስተሳስሩ ፕሮጀክቶች መቀረጽ አለባቸው ማለቱ ይታወሳል።
የሱዳን የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ በዚህ ጉባኤ ላይ እንዳሉት የምስራቅ ናይል ተፋሰስ አባል አገራትን የሚጠቅሙ የጋራ ፕሮጀክቶችን ቀርጸን ወደ ስራ መግባት አለብን በሚል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በዚህ ጉባኤ ላይ አገራቱን የሚያስተሳስሩ የጋራ ፕሮጀክቶችን መቅረጽ እንደሚገባ ገልጸው ለአብነትም የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ህዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ የባሮ-አኮቦ ወንዝ ፕሮጀክቶችን መቅረጽ ይቻላል በሚል በዚህ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።
የምስራቃዊ ናይል ተፋሰስ አገራት ጉባኤ ወይም ኢንትሮ የሚባለው ተቋም ኢትዮጵያ፤ሱዳን፤ደቡብ ሱዳን እና ግብጽን በአባልነት የያዘ ሲሆን ጉባኤውን ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በዚህ ጉባኤ ላይ ከግብጽ ውጪ የሶስቱ አገራት ውሃ እና መስኖ ሚኒስትሮች ተገኝተው በውሃ እና ተፋሰስ ሀብት የጋራ ጥበቃ እና ልማት ላይ መክረዋል።