“ሁለተኛው ዙር የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት የግድ ይካሄዳል” ዶ/ር ስለሺ በቀለ
የምስራቅ ናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
“ግድቡ በታቀደው ልክ ባለመገንባቱ የተባለውን ያህል ውሃ አይዝም“ በሚል የሚነሱ ሀሳቦችን ሚኒስትሩ አጣጥለዋል
ሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን በማስመልከት ሰሞኑን ከግብፅ እና ከሱዳን የሚወጡ መረጃዎች “ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ባቀደችው ልክ ሳታካሂድ ክረምቱ ስለሚገባ ግድቡ የተባለውን ያህል ውሃ መያዝ አይችልም” እያሉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ እነዚህን ከግብፅ እና ከሱዳን የሚወጡ ሀሳብ ውድቅ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፣ ግድቡ በአሁኑ ክረምት “የግድ የተባለውን የውሃ መጠን” ማለትም 13.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይይዛል ብለዋል፡፡ ይህም ከተሳካ ግድቡ ከመጀመሪያው ዙር ጋር ተደምሮ 18 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይይዛል ማለት ነው፡፡ “ሁለቱ ተርባይኖችም ኤሌክትሪክ ያመነጫሉ” ሲሉ ሚኒስትሩ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
የሱዳን ውሃ እና መስኖ ሚንስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባቷን እና ውሃውን መጠቀሟን ሱዳን እንደማትቃወም ገልጸው፣ ነገር ግን ከውሃው ሙሌት እና አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ የመረጃ ልውውጥ መኖር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው ከሕሴው ግድብ 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሱዳን የሚገኘውን “ሮሳሬስ ግድብን ለማስተዳደር የሕዳሴው ግድብ መረጃ ያስፈልጋል ፤ ያለበለዚያ በግድቡ ውሃ ለመያዝ እና ለመልቀቅ እንቸገራለን” የሚል ነው፡፡
ከግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ እና የሱዳን የውሃ ዘርፍ ሚኒስትሮች አስተያየታቸውን የሰጡት፣ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው የምስራቅ ናይል ተፋሰስ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው፡፡
ሱዳን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ጊዜያዊ ውል ማድረግ እንደምትፈልግ የሀገሪቱ ውሃና መስኖ መስኖ ሚኒስትሩ ፕ/ር ያሲር ትናንት ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም በካርቱም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ሱዳን ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ “ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን ሙሌት ካካሄደች በኋላም ቢሆን ድርድሩ እንዲቀጥል” የሚጠይቅ መሆኑን ሚኒስትሩ ወደ አዲስ አበባ ከማቅናታቸው በፊት በሰጡት መግለጫ ላይ አንስተዋል።
በዚህም ሱዳን ቀድሞ ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ መፈራረምን ጨምሮ ቅድመ ሁኔታውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚደረጉ ጊዜያዊ ስምምነቶችን እንደምትቀበል ሚንስትሩ ተናግረዋል።
የምስራቅ ናይል ተፋሰስ ጉባኤ አባል የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በአዲስ አበባ እየተወያዩ ይገኛል፡፡
ግብፅ የጉባኤው አባል ብትሆንም በጉባኤው አልተሳተፈችም፡፡ ከግብፅ በኩል ሚንስትርም ሆነ ባለሙያ አለመገኘቱ ታውቋል፡፡
የዚህ ጉባኤ ዋና ዓላማ የምስራቅ ናይል ተፋሰስ ውሃ ሚንስትሮች ተፋሰሱን ማልማት በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ መወያየት እና በሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሆነ የኢትዮጵያ ውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚንስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጉባኤ የሕዳሴው ግድብ አጀንዳ አይሆንም ተብሏል፡፡