ስፔን የ16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮኗን ጣሊያን በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ተቀላቀለች
ጣሊያን 16ቱን ለመቀላቀል የፊታችን ሰኞ ክሮሽያን ማሸነፍ ይጠበቅባታል
ከምድብ አራት ፈረንሳይ ከኔዘርላንድስ ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
ስፔን ጀርመን እያስተናገደችው በምትገኘው የአውሮፓ ዋንጫ ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏን አረጋግጣለች።
ጣሊያናዊው የቦሎኛ ክለብ ተከላካይ ሪካርዶ ካላፊዮሪ በ55ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠራት ጎል ነው ስፔን 1 ለ 0 ያሸነፈችው።
ማራኪ ጨዋታ ያሳየው የስፔን ብሄራዊ ቡድን በርካታ የግብ እድሎችን ቢፈጥርም የጣሊያኑን ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማ የሚፈታተኑ አልሆኑም።
የምሽቱን ውጤት ተከትሎም ስፔን በስድትስ ነጥብ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለች ሲሆን፥ ከጀርመን በመቀጠል 16ቱ ውስጥ መግባቷን ያረጋገጠች ሀገር ሆናለች።
በኮሮና ምክንያት ዘግይቶ በ2021 የተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ያነሳችው ጣሊያን ከምድብ ሁለት በ3 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
የሉሲያኖ ስፓሌቲ ቡድን የፊታችን ሰኞ ክሮሽያን ማሸነፍ ከቻለ በቀጥታ ጥሎ ማለፉን ያረጋግጣል።
የሉካ ሞድሪቿ ክሮሽያ ደግሞ ጣሊያንን አሸንፎ የአልባኒያን በስፔን መሸነፍ አልያም አቻ መውጣት ይጠባበቃል።
የ17ኛው የአዎፓ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ ፈረንሳይ ከኔዘርላንድስ ምሽት 4 ስአት ላይ ይፋለማሉ።
በፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ የተሸነፉት ፖላንድ እና ኦስሪያ ቀደም ብለው 1 ስአት ላይ ይጫወታሉ።
በምድብ አምስት የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን በሮማኒያ 3 ለ 0 የተሸነፈችው ዩክሬን ቀን 10 ስአት ላይ ስሎቬኒያን ትገጥማለች።
በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ቤልጂየምን 1 ለ 0 የረታችው ስሎቪኒያ ከሮማኒያ እኩል ሶስት ነጥብ ያላት ሲሆን ዛሬ ዩክሬንን ካሸነፈች ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏን ታረጋግጣለች።
በአውሮፓ ዋንጫ ከየምድባቸው 1ኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ 12 ቡድኖችና አራት ምርጥ ሶስተኛ ቡድኖች ጥሎ ማለፉን እንደሚቀላቀሉ ይታወቃል።