አስፈሪ የሚባለው ነብር 4 ሺህ 600 እንዲሁም ድኩላ ደግሞ 6 ሺህ ዶላር ዋጋ ለአደን ተቀምጦላቸዋል
የዱር እንስሳት አደን ክፍያ ተመን በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ለሕጋዊ አደን የተፈቀዱ እና ያልተፈቀዱ የዱር እንስሳት ያሏት ሲሆን አንበሳ፣ ነብር፣ የደጋ አጋዘንን ጨምሮ በአጠቃላይ 54 የዱር እንስሳት ለአደን ተፈቅደዋል፡፡
እንዲሁም ዋልያ፣ ዝሆን፣ ተኩላ፣ አውልድጌሳን ጨምሮ 48 የዱር እንስሳት ደግሞ ለአደን ከተከለከሉት መካከል ዋነኞቹ መናቸውን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት፣ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት አጠቃቀም ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ወርቁ ለአል ዐይን እንዳሉት ለአደን የተፈቀዱት የዱር እንስሳዎች በተቀመጠላቸው መስፈርቶች መካከል ጾታው ወንድ የሆነ፣ ያረጀ እና በህይወት ቢቆይ ስነ ህይወታዊ ጥቅሙ አነስተኛ የሆነ የዱር እንስሳ ለአደን ይዘጋጃል፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን የዱር እንስሳት ለማደን ዝቅተኛው 50 ዶላር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 15 ሺህ ዶላር ክፍያን እንደምታስከፍል አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
ዝቅተኛ ክፍያ ከሚከፈልባቸው ሕጋዊ አደኖች መካከል ጃርት አንዷ የዱር እንስሳት ስትሆን የደጋ አጋዘን ደግሞ 15 ሺህ ዶላር ክፍያ ተጥሎበታል፡፡