ሩሲያ በኩርስክ ግዛት ውጊያ ለመክፈት 50ሺ ወታደሮችን ማዘጋጀቷን ዘለንስኪ ገለጹ
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ድንበር በመጣስ በምዕራብ ሩሲያ ጥቃት እየፈጸመ ያለው የዩክሬን ጦር አሁን ላይ ከ50ሺ ወታደሮች ጋር ሊዋጋ መሆኑን ገልጸዋል
የሩሲያ ኃይሎች በግዛቱ ወሳኝ የሎጂስቲክ ማመላለሺያ ወደሆነችው የፖክሮቭስክ ከተማ ቀስ እያሉ እየገለፉ ናቸው
ሩሲያ በኩርስክ ግዛት ውጊያ ለመክፈት 50ሺ ወታደሮችን ማዘጋጀቷን ዘለንስኪ ገለጹ።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ድንበር በመጣስ በምዕራብ ሩሲያ ጥቃት እየፈጸመ ያለው የዩክሬን ጦር አሁን ላይ ከ50ሺ ወታደሮች ጋር ሊዋጋ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘለንስኪ በሰጡት እለታዊ መግለጫ እንደተናገሩት ዘመቻው ሞስሶ በዩክሬን ውስጥ ያላትን የማጥቃት አቅም ቀንሷታል። ፕሬዝደንቱ የጥቃቱ አላማ ይህ መሆኑን ለረጅም ጊዜ ሲገጹ ቢቆዩም የተወሰኑ ምዕራባውያን አጋሮቻቸው ግን በጥርጣሬ ነው የሚያዩት።
ሮይተርስ የአሜሪካ መንግስታዊ ያልሆነ የጦር ጥናት ኢንስቲትዩቱ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ዩክሬን በነሐሴ መጀመሪያ ላይ አስደንጋጭ የተባለውን ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት ሩሲያ በኩርስክ ግዛት የነበራት 10ሺ ወታደሮች ብቻ ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ያለውን ኃይሏን ሳታስወጣ በኩርስክ ግዛት ያለውን ኃይሏን ማጠናከሯን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
አይቀሬ ለሆነው የሩሲያ መልሶ ማጥቃት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችም ተሰማርተዋል ተብሏል። ዘለንስኪ በንግግራቸው የዩክሬን ጦር አዛዥ ጀነራል ኦሌክሳንደር ስሪስኪ በኩርስክ ግዛት ስለተሰለፈው ጦር መረጃ እንደሰጧቸው ገልጸዋል።
" የዩክሬን ጦር በኩርስክ ግዛት ምክንያት ወደ ሌላ የዩክሬን ክፍል መንቀሳቀስ ያልቻሉ 50ሺ የወራሪ ወታደሮችን ወጥሮ ይዟል" ብለዋል ዘለንስኪ።
ጀነራል ስሪስኪ እንዳሉት የዩክሬን ጦር በኩርስክ ጥቃት ባይፈጽም ኖሮ "በ10ሺዎች የሚቆጠሩት ምርጥ የሚባሉት የሩሲያ አጥቂ ሰራዊት ቡድኖች በዶኔስክ ግዛት ያሉ ምሽጎታችን ይደረምሱ ነበር።"
ሁለቱ ወገኞች በዩክሬን ቁጥጥር ስር ባለችው ኩራከሰሆቭ ከተማ አቅራቢያ ባለ ግድብ ላይ ጥቃት በማድረስ በሚካሰሱበት ዶኔስ ግዛት ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
የሩሲያ ኃይሎች በግዛቱ ወሳኝ የሎጂስቲክ ማመላለሺያ ወደሆነችው የፖክሮቭስክ ከተማ ቀስ እያሉ እየገለፉ ናቸው። ኒው ዮርክ ታይምስ በስም ያልጠቀሳቸውን የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣናት ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ሩሲያ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ጨምሮ 50ሺ ወታደሮችን በኩርስክ ግዛት አዘጋጅታለች።
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ባለፈው ሐምሌ ወር ኪም እና ፑቲን የፈረሙትን የመከላከያ ስምምነት አጽድቀውታል።
ስምምነቱ ከሁለቱ በአንደኛቸው ላይ ጥቃት በሚደርስበት ወቅት አንዳቸው ሌላኛቸው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን ሀገራት ሰሜን ኮሪያ በዩክሬኑ ጦርነት ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ልካለች የሚል ክስ አቅርበዋል። ሩሲያ ይህን ክስ በቀጥታ አላስተባበለችም፤ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ግዛቷ ማስገባቷንም አላመነችም።