ኢራን፤ እስራኤል ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንድትታገድ ጠየቀች
ቴህራን ጥያቄውን ያቀረበችው ሰሞኑን በደማስቆ በተፈጸመ ጥቃት ንጹሀን መገዳለቸውን ተከትሎ ነው
በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የሚገኘውን ውጥረት ተከትሎ የተመድ እና የእስራኤል ግንኙነት እንደሻከረ ይነገራል
እስራኤል ከመንግስታቱ ድርጅት አባልነት እንድትሰናበት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋሂ አለም አቀፋዊ ህጎችን በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እየጣሰች የምትገኘው ቴል አቪቭ ከአለም አቀፉ ተቋም መገለል አለባት ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በመካከለኛው ምስራቅ የሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋቶች እንደጨመሩ በመግለጽ፥ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የእስራኤልን ህገወጥ ተግባራት አይቶ እንዳላየ ከማለፍ ሊቆጠብ እንደሚገባ ነው ያስጠነቀቁት፡፡
ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት ባሳለፍነው እሁድ እስራኤል በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ንጹሀን መገደላቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የአውሮፓ እና የአሜሪካ ያልተገደበ ድጋፍ እስራኤል በህገወጥ ተግባሯ እንድትገፋ አረንጓዴ መብራት ሰጥቷል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በፍልስጤም፣ ሊባኖስ እና ሶሪያ የሚደርሰው ያልተገባ የንጹሀን ግድያ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
“በጽዮናዊው አገዛዝ ላይ ተግባራዊ እና ውጤታማ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል፤ ይህም የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መጣልን፣ አገዛዙን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማባረርን ጨምሮ መሪዎቹን መከሰስ እና መቀጣትን ማካተት አለበት” ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።
እስራኤል ከተቆጣጠረቻቸው የጎላን ኮርብቶች የተነሱ ናቸው የተባሉ የጦር አውሮፕላኖች በደማስቆ “ሳይዳ ዛይናብ” በተባለ አካባቢ በመኖርያ ህንጻ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የሶርያ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡
የእስራኤል ጦር እስካሁን ለጥቃቱ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
በባለፈው ወር መጨረሻ ማሌዢያ እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ እያደረሰች በምትገኘው በደል ከተመድ እንድትሰናበት የሚጠይቅ ረቂቅ ሰነድ ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርባ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በጋዛ እና ሊባኖስ ጦርነት አለፍ ሲልም በመካከለኛው ምስራቅ እያየለ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ እስራኤል ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እየሻከረ መጥቷል፡፡
በጥቅምት ወር መጀመሪያ ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን ጥቃት አላወገዙም የተባሉት የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ እስራኤል እንዳይገቡ ታግደው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ጉቴሬዝ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በመላው መካከለኛው ምስራቅ እየተስፋፋ የመጣውን ግጭት እቃወማለሁ” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ከ100 በላይ ሀገራት ይህን የእስራኤል ውሳኔ በመቃወም ባወጡት መግለጫ እርምጃው ተመድ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በነጻነት ተንቀሳቅሶ እንዳያከናውን የሚያግድ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ኢራን አሁን ባቀረበችው ጥያቄ ጉዳዮን ይፋዊ በሆነ መንገድ ለመንግስታቱ ድርጅት ልታቀርበው እንደምትችል የታወቀ ነገር ባይኖርም እስራኤል ከድርጅቱ እንድትታገድ በመጠየቅ ከማሌዥያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ሀገር ሁናለች፡፡