በቻይና ከሚስቱ ጋር የተፋታ ግለሰብ የ35 ሰዎችን ህይወት አጠፋ
ግለሰቡ መሬት ላይ ስፖርት በሚሰሩ ግለሰቦች ላይ ተሽከርካሪውን በፍጥነት በመንዳት ከ40 በላይ ሰዎችንም ማቁሰሉ ተገልጿል
ፖሊስ አሰቃቂውን ጥቃት የፈጸመው የ62 አመት አዛውንት ራሱን በቢላ በመውጋት ላይ እያለ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል
በደቡባዊ ቻይና ዡሃይ በተሰኘች ከተማ በተሽከርካሪ የተፈጸመ ጥቃት የ35 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
በከተማዋ ከህንጻ ውጭ መሬት ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ተሽከርካሪውን በፍጥነት የነዳው ግለሰብ 43 ሰዎችን ማቁሰሉንም የከተማዋ ፖሊስ ገልጿል።
በመሬት ላይ ተንጋለው ስፖርት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች በተሽከርካሪ ሲገጩ የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ተለቀዋል።
ሬውተርስ እንደዘገበው ጥቃቱ ሲፈጸም በርካቶች “ሽብርተኛ” እያሉ ሲያለቅሱ ይደመጡ የነበረ ሲሆን፥ አምቡላንሶችም በፍጥነት ደርሰው የተጎዱትን ወደ ሆስፒታል ሲወስዱ ታይተዋል።
"ፋን" የሚለው የቤተሰቡ ስም ብቻ የተጠቀሰው ጥቃት አድራሽ ለማምለጥ ሲሞክር በፖሊስ መያዙም ተዘግቧል።
አንገቱን ደጋግሞ በቢላ የወጋው ግለሰብ ከባለቤቱ ጋር በፈጸመው ፍቺ በመበሳጨቱ ጥቃቱን መፈጸሙን የፖሊስ ቅድመ ምርመራ አመላክቷል።
ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በአሰቃዊው ጥቃት የተጎዱ ሰዎች በፍጥነት ተገቢው ህክምና እንዲደርግላቸውና ጥቃት አድራሾች ከባድ ቅጣት እንዲተላለፍባቸው ማሳሰባቸውን ሲሲቲቪ ዘግቧል።
የሀገሪቱ ማዕከላዊ መንግስት ጥቃቱን በተመለከተ የሚካሄደውን ምርመራ የሚያግዝ ቡድን ወደ ዡሃይ ከተማ መላኩም ነው የተገለጸው።
ቻይና በዡሃይ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ግዙፍ የአየር ትርኢት በማሳየት ላይ ትገኛለች። በዚህ ትርኢትም ቤጂንግ ያመረተችውና ምዕራባውያኑን ይገዳደራል የተባለውን “ጄ-35ኤ” ጄት አሳይታለች።
ጠንካራ የደህንነት ተቋማት በገነባችውና ጥብቅ የጦር መሳሪያ ህግ ባላት ቻይና መሰል በርካቶችን የሚቀጥፉ ወንጀሎች አልተለመዱም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በትልልቅ ከተሞች በስለት የሚፈጸሙ ጥቃቶች መበራከት ህዝብ የሚሰብሰብባቸው ስፍራዎችን ደህንነት ጥያቄ ውስጥ እየከተቱ ነው።
በጥቅምት ወር 2024 በቤጂንግ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አቅራቢያ በስለት የተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎችን ማቁሰሉ ይታወሳል።
በመስከረምም በሻንጋይ በሚገኝ የገበያ ማዕከል በስለት ጥቃት ሶስት ሰዎች መገደላቸውና 15 ሰዎች መቁሰላቸው አይዘነጋም።