ስዊድን በአለማችን ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ የሚገኘውን ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ልትሸልም ነው
ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ ለ23 አመት አመት በኤርትራ ያለምንም የክስ ሂደት በእስር ይገኛል ተብሏል
ዳዊት በኤርትራ የመጀመሪያውን የግል ጋዜጣ “ሰቲት” ካቋቋሙ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው
በኤርትራ ከ23 አመት በላይ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ የስዊድን የሰብአዊ መብት ሽልማት ሊበረከትለት ነው።
ጋዜጠኛው የንግግር ነጻነት እንዲከበር ላደረገው ትግል ነው “ኤደልስማን” የተሰኘው ሽልማት የተበረከተለት።
የሽልማቱ አዘጋጅ ተቋም ዳዊት ኢሳቅ “ልዩ ቁርጠኝነት ያለው” ጋዜጠኛ መሆኑን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ጋዜጠኛ ዳዊት የኤርትራ እና ስዊድን ጥምር ዜግነት ያለው ሲሆን፥ በኤርትራ የመጀመሪያ የሆነችውን “ሰቲት”ጋዜጣ ካቋቋሙት መካከል አንዱ ነው።
በጋዜጣዋ ላይ በኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ለውጦች እንዲደረጉ የሚጠይቅ ጽሁፍ በመታተሙ በፈረንጆቹ 2001 በቁጥጥር ስር መዋሉንም ቢቢሲ ዘግቧል።
ዳዊት ከበርካታ ሚኒስትሮች፣ የፓርላማ አባላት እና ጋዜጠኞች ጋር በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የት እንደሚገኝ እና ስለጤናው ሁኔታ የሚታወቅ ነገር የለም። አብዛኞቹ ከዳዊት ጋር የታሰሩት ህይወታቸው እንዳለፈ እንደሚታመን ዘገባው ጠቅሷል።
ስዊድን የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅን እንዲለቅና የሚገኝበትን ሁኔታ እንዲያሳውቃት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርባ ምላሽ አላገኘችም።
“ዳዊት በአለማችን ያለምንም ክስና የጥፋተኝነት ፍርድ ለረጅም ጊዜ የታሰረ ጋዜጠኛ ነው፤ የሚገኝበት የጤና ሁኔታ እና የታሰረበትን ስፍራ ማወቅ አለመቻላችን ያሳስበናል፤ ወላጆቹንም ሆነ የህግ ድጋፍ እንዲያገኝ አልተፈቀደም፤ በግድጃ እንዲሰወር ተደርጓል” ይላሉ የ”ኤድልስታም” ሽልማት የዳኞች ቡድን ሊቀመንበር ካሮሊን ኤደልስታም።
አለማቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ ለ23 አመት የታሰረውን ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ እንድትለቅ ጫና እንዲያደርግባትና የሰብአዊ መብት እንድታከብር ጫና ያደርግባት ዘንድም ጠይቀዋል።
በስዊድናዊው ዲፕሎማት ሃራልድ ኤደልስታም ስም የተሰየመው የ”ኤድልስታም” ሽልማት ለሰብአዊ መብት መከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የሚሰጥ ነው።
የዳዊት እህት ቤተልሄም ኢሳቅ በስቶኮልም ከሰባት ቀናት በኋላ ሽልማቱን ትቀበልለታለች ተብሏል።
ኤርትራ የግል መገናኛ ብዙሃን “ለብሄራዊ ደህንነቴ አስጊ ናቸው” በሚል በፈረንጆቹ 2001 ዘግታቸዋለች፤ ይህም አስመራን አንድም የግል ሚዲያ የሌለባት ሀገር አድርጓታል።