ኢትዮጵያ ለአንድ ሕጋዊ የዱር እንስሳት አደን እስከ 15 ሺህ ዶላር እንደምታስከፍል ያውቃሉ?
ጃርትን ጨምሮ አንበሳ፣ ነብር እና የደጋ አጋዘን ለማደን የሚፈልጉ ጎብኚዎች ከ50 ዶላር እስከ 15 ሺህ ዶላር መክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል
ኢትዮጵያ የሕጋዊ አደን ዋጋ ውድ ከሆኑባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ናት
ኢትዮጵያ ለሕጋዊ የዱር እንስሳት አደን እስከ 15 ሺህ ዶላር እንደምታስከፍል ያውቃሉ?
የዱር እንስሳትን ማደን የሚፈልጉ ጎብኚዎች በመላው ዓለም ያሉ ሲሆን አፍሪካ ዋነኛ የዱር እንስሳት አዳኞች መዳረሻ ናት፡፡
ናሚቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክ እና ደቡብ አፍሪካ ዋነኛ የዱር እንስሳት ማደንን በሚፈልጉ ጎብኚዎች የሚጥለቀለቁ ሀገራት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም የዱር እንስሳትን ለህጋዊ አደን ከሚያዘጋጁ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ለዚህ የሚረዳ አሰራር መዘርጋቷን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት አጠቃቀም ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ወርቁ ለአል ዐይን እንዳሉት ኢትዮጵያ በአራት ክልሎች ሕጋዊ የዱር እንስሳት አደን በማካሄድ ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ክምላው ዓለም ለሚመጡ ጎብኚዎች ሕጋዊ የዱር እንስሳት አደን እየተካሄደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለሕጋዊ አደን የተፈቀዱ እና ያልተፈቀዱ የዱር እንስሳት ያሏት ሲሆን አንበሳ፣ ነብር፣ የደጋ አጋዘንን ጨምሮ በአጠቃላይ 54 የዱር እንስሳት ለአደን ተፈቅደዋል፡፡
እንዲሁም ዋልያ፣ ዝሆን፣ ተኩላ፣ አውልድጌሳን ጨምሮ 48 የዱር እንስሳት ደግሞ ለአደን ከተከለከሉት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ ለአደን የተፈቀዱት የዱር እንስሳዎች በተቀመጠላቸው መስፈርቶች መካከል ጾታው ወንድ የሆነ፣ ያረጀ እና በህይወት ቢቆይ ስነ ህይወታዊ ጥቅሙ አነስተኛ የሆነ የዱር እንስሳ ለአደን ይዘጋጃል፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን የዱር እንስሳት ለማደን ዝቅተኛው 50 ዶላር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 15 ሺህ ዶላር ክፍያን እንደምታስከፍል አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
ዝቅተኛ ክፍያ ከሚከፈልባቸው ሕጋዊ አደኖች መካከል ጃርት አንዷ የዱር እንስሳት ስትሆን የደጋ አጋዘን ደግሞ 15 ሺህ ዶላር ክፍያ ተጥሎበታል፡፡
እንዲሁም መስፈርቶቹን አሟልቶ ለሚመጣ ጎብኚ አዳኝ ከተፈቀደለት የዱር እንስሳ ውጪ ከገደለ ለአደን የከፈለው ክፍያ እጥፍ እንዲከፍል ይገደዳል ሲሉ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን ለስድስት የዱር እንስሳት አሳዳኝ የግል ድርጅቶች ፈቃድ የሰጠች ሲሆን የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች በኢትዮጵያ የዱር እንስሳትን ለማደን ፍላጎት ካላቸው በነዚህ አሳዳኝ ድርጅቶች በኩል ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የቱሪዝም ሚንስቴር የ31 ሆቴሎችን ኮኮብ ደረጃ ይፋ አደረገ
አስፈሪ የዱር እንስሳት ከሚባሉት መካከል ነበር እና አንበሳም ለህጋዊ አደን የሚዘጋጁ ሲሆን አንድ አንበሳን ለማደን 4 ሺህ ዶላር እንዲሁም ነብርን ለማደን ደግሞ 4 ሺህ 600 ዶላር መክፈል በግዴታነት ተቀምጧል ተብሏል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ የአደን ጎብኚዎች መካከል 90 በመቶዎቹ የደጋ አጋዘንን ለማደን የሚመጡ እንደሆኑ ሃለፊው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ባሉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከሕጋዊ የዱር እንስሳት አደን 90 ሚሊዮን ብር እንዳገኘች ተገልጿል፡፡
ይሁንና በኢትዮጵያ ያሉት የጸጥታ ችግሮች ጎብኚዎች እንደልብ እንዳይንቀሳቀሱ እና የታሰበውን ያህል ጥቅም እንዳይገኝ ማድረጉን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
አሁን በስራ ላይ ያለው የዱር እንስሳት ሕጋዊ አደን አዋጅ በ2001 ዓም የወጣ በመሆኑ የወቅቱን ዋጋ ያላገናዘበ ነው በሚል የዋጋ ማሻሻያ ለማድረግ አዋጁ በመሻሻል ላይ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል በተለይም ዝቅተኛው የዱር እንስሳት አደን ክፍያ 100 ዶላር እንዲሆን እንዲሁም የፓርኮች መግቢያ ዋጋ እንዲሻሻል እየጠየቁ መሆናቸውንም ታግረዋል፡፡