የትራምፕ የነጩ ቤት የመጀመሪያ ቀን እና የህገወጥ ስደተኞች እጣ ፈንታ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ህገወጥ ሰደተኞችን ከሀገር ለማባረር የሚያስችሉ የመመርያ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል
ትራምፕ በመጀመሪያው ዙር እስከ 1 ሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞችን ከሀገር ሊያስወጡ ይችላሉ ተብሏል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በነጩ ቤት የመጀመርያ ቀን የስልጣን ቆይታቸው ከህገወጥ ስደተኞች ጋር በተያያዘ ወሳኝ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚችሉ ተሰምቷል፡፡
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት እና ቀደም ብሎ በነበራቸው የስልጣን ዘመን ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ጠንካራ ፖሊሲ እንደሚከተሉ ይታወቃል፡፡
ከጥር 20 በኋላ በስልጣናቸው የመጀመርያ ቀን ሶስት ትላልቅ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፉ ሮይተርስ ከጉዳዮ ጋር ቅርበት ያላቸው ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የሜክሲኮን ድንበር ግንብ ድጋሚ ማስጀመር ፣ በድንበሮች ላይ የሚሰማሩ የብሔራዊ ዘብ ሰራዊቶችን ቁጥር መጨመር እንዲሁም ባይደን ስደተኞች በህጋዊ መንገድ እንዲገቡ አስጀምረውት የነበረውን ማዕቀፍ መሰረዝ ፕሬዝዳንቱ ከሚተገብሯቸው እርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ትራምፕ በነጩ ቤት የመጀመርያ ቀን የስራ ጊዜያቸው የስደተኞች አጀንዳቸውን ለማስፈጸም በሚወስዱት እርምጅ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከሀገር ሊያስወጡ ይችላሉ፡፡
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት እስከ 2023 መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ የሀገሪቱን የህዝብ ቁጥር 3.3 በመቶ የሚሸፍኑ (11.7 ሚሊየን )ህገወጥ ስደተኞች እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል፡፡
ኒውዮርክ ፣ ቺካጎ እና ዴንቨርን የመሳሰሉ ከተሞች ለስደተኞች የቤት ፣ የምግብ እና የህክምና ወጪዎችን ለመሸፈን በአመት በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርጉ ተዘግቧል፡፡
የኢሜግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተቋማት ከህገ ወጥ ስደተኞች ጋር በተያያዘ ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸውን ጨምሮ ሌሎች ስደተኞችን ከሀገር ማስወጣት የሚችሉበትን መመሪያ ቀለል ማድረግ ትራምፕ ይከተሉታል ተብለው ከሚጠበቁ አሰራሮች መካከል አንዱ ነው፡፡
በአንጻሩ ህገ ወጥ ስደተኞች የመስሪያ እና የመኖርያ ፈቃድ የሚያገኙበትን ህግ በማጥበቅ ስደተኞችን ለማሰር እንዲሁም ለማባረር ሙሉ መንግስታዊ አካሄድን እንደሚጠቀሙም ተገልጿል፡፡
ለዚህም በህገ ወጥ ስደተኞች ዙርያ በፕሬዝዳንቱ ልክ ጠንካራ አቋም ያላቸውን በቀድሞ አስተዳደራቸው ውስጥ የነበሩ እና ሌሎች አዳዲስ ሀላፊዎችን በመሾም ላይ ይገኛሉ፡፡
በጆ ባይደን አስተዳደር ከባድ የወንጀል ሪከርድ ያለባቸው ስደተኞች እንዲታሰሩ እና ህጋዊ የመኖርያ ፈቃድ ለማግኝት የጀመሩት ሂደት እንዲቋረጥ የተወሰነባቸው አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞች በመጀመርያው ዙር ወደ መጡበት የሚመለሱ ስደተኞች ናቸው፡፡
የሮይተርስ ምንጮች እንደተናገሩት ሀማስን የሚደግፉ አለም አቀፍ ተማሪዎች የትምህርት ቪዛቸው ተሰርዞ በመጀመርያው ዙር ከሀገር ከሚወጡ ስደተኞች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
ስደተኞችን ከሀገር ለማባረር በሚኖረው ጥረት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ፣ ከአጋር የመንግስት ኤጄንሲዎች ድጋፍን በመጠየቅ እና ሁሉንም የትራንስፖርት አማራጮች ሊጠቀም ይችላል ተብሏል፡፡
የፕሬዝዳንቱ የስልጣን ሽግግር ጊዜ ገና በጅምር ላይ እንደመሆኑ በአለ ሲመታቸው እስከሚፈጸምበት ጥር 20 ድረስ የእቅድ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተጠባቂ ቢሆንም፤ በስደተኞች ጉዳይ በፖሊሲ ደረጃ እምብዛም የሚቀየር ነገር አለመኖሩን ምንጮቹ ተናግረዋል ።