የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን የጫናቸው ጦር መሳሪያዎች “ህጋዊ የአደን ጦር መሳሪያዎች” መሆናቸውን አስታወቀ
ይህን የሚያረጋገጡ እና ከሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጭምር ያገኘኋቸው ህጋዊ የሰነድ ማረጋገጫዎች አሉኝም ነው አየር መንገዱ ያለው
አየር መንገድ ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ፈቃድ ካገኘ በኋላ መሳሪያዎቹን መጫኑን አስታውቋል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጦር መሳሪያዎችን በህገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን አስገብቷቸዋል በሚል በሱዳን ዜና አገልግሎት (ሱና) ለቀረበበት ዘገባ ምላሽ ሰጠ፡፡
ጦር መሳሪያዎቹ በህጋዊ መንገድ ፈቃድ አግኝተው ወደ ሱዳን የገቡ ናቸው ያለው አየር መንገዱ በተገቢ የስምምነት ሰነዶች በአደራ የተረከብኳቸው የአደን ጦር መሳሪያዎች ናቸው ሲል አስታውቋል፡፡
የአደን ጦር መሳሪያዎቹ በኢትዮጵያ የደህንነት አካላት ተይዘው ለረዥም ጊዜያት በአዲስ አበባ መቆየታቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡
በዚህም ወደ ሱዳን እንድጭንለት በአደራ ሰጥቶኝ የነበረው አካል ‘ጦር መሳሪያዎቹን ያጓጉዝ አለበለዚያም 250 ሺ የአሜሪካ ዶላር ካሳ ይክፈለኝ’ ሲል በሱዳን ፍርድ ቤቶች ከሶኝ ነበርም ብሏል፡፡
ሆኖም ሁኔታዎችን ካጣሩ የኢትዮጵያ ደህንነት አካላት ፈቃድ ባገኘ ጊዜ ጦር መሳሪያዎቹን ወደ ሱዳን መጫኑንም ነው አየር መንገዱ የገለጸው፡፡
የዚህን ህጋዊነት የሚያረጋገጡ እና ከሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጭምር ያገኘኋቸው ህጋዊ የሰነድ ማረጋገጫዎች አሉኝም ብሏል፡፡
የተባሉት ጦር መሳሪያዎች ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ነው በካርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚገኙ የጉምሩክ ሰራተኞች የተያዙት እንደ ሱና ዘገባ፡፡
መሳሪያዎቹ ከአዲስ አበባ ወደ ካርቱም ባቀና እና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆነ አውሮፕላን ተጭነውም ነበረ፡፡
በአል በሽር የአገዛዝ ዘመን ተበዝብዘዋል የተባሉ ሃብቶችን ለማስመለስ የተቋቋመው ኮሚቴም ነው ስለ ጦር መሳሪያዎቹ በማጣራት ላይ ያለው፡፡
“መሳሪያዎቹ ከሩሲያ ሞስኮ የተገዙ ናቸው”ያሉት የኮሚቴው አባል ወግዲ ሳሌህ በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት መቆየታቸውን ካርቱም ለሚገኘው የአል ዐይን ኒውስ ዘጋቢ ተናግረዋል፡፡
የምሽት ባይኖኩላር መነጽሮችን ጨምሮ 72 ሳጥን አውቶማቲክ ጥይቶች መያዛቸውንም ነው ሳሌህ የተናገሩት፡፡
ጦር መሳሪያዎቹ ምናልባትም የሃገሪቱን የሽግግር ጉዞ ለማደናቀፍ የገቡ ናቸው በሚል መያዛቸውንም ገልጸዋል፡፡
ምርመራው ሲጠናቀቅ ሙሉ መረጃን እንሰጣለንም ብለዋል ሳሌህ፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ከሱዳን የተነሱ የሽብር ቡድን አባላትን መደምሰሱን ከሰሞኑ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡