ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታካሄዳለች
አንድ ሚሊየን መራጮች የሚሳተፉበት የነገው ምርጫ በራስ ገዟ ሀገር ታሪክ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው
አሁናዊ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቤሂ ከሁለት እጩዎች ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሏል
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታካሄዳለች።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በነገው እለት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ልታካሄድ ነው፡፡
አሁናዊውን ፕሬዝዳንት ሙሴ ቤሂ አብዲን ጨምሮ ሶስት ተፎካካሪዎች ሀገሪቱን ለመምራት እጩ ሆነው ቀርበዋል፡፡
ከ2017 ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩት እና ለሁለተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመን የሚወዳደሩት ሙሴ ቤሂ የሶማሊላንድን ዲሞክራሲ ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ እድገትን ለማሻሻል እንዲሁም የሀገርነት እውቅናን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ከአሜሪካ ድምጽ ጋር በነበራቸው ቆይታም ፕሬዝዳንት ሆነው የሚመረጡ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈረመውን የወደብ የመግባብያ ስምምነት ወደ ተግባራዊነት እንደሚያስገቡ ተናግረዋል፡፡
"በእኛ በኩል ስምምነቱን ለመተግበር ነጻ እና ዝግጁ ነን፤ እየተጠባበቅን የምንገኘው ከኢትዮጵያ በኩል የሚመጣውን ምላሽ ነው፤ እርሱን ካገኝን ወደ ትግበራ የማንገባበት ምክንያት አይኖርም" ብለዋል፡፡
አብዱራህማን መሀመድ አብዱላሂ ከዋዳኒ ፓርቲ፣ ፋይሰል አሊ ዋራቢ ከፍትህ እና እድገት ፓርቲ ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ሌሎቹ ዕጩዎች ናቸው፡፡
ሃርጌሳ የራሷ ፓስፖርት ፣ የመገበያያ ገንዘብ ፣ የጸጥታ ሀይሎች ፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚያስገድድ የፖለቲካ ስርአት ብትከተልም ለ33 አመት ሙሉ የሀገርነት እውቅና ሳታገኝ ቆይታለች፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ አሁንም ጋዜጠኞች እና ማህበራዊ አንቂዎች ከባለስልጣናት ጫና ይደርስባቸዋል ፤ አናሳ ጎሳዎች ለፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መገለል የተጋለጡ ሲሆኑ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ቢሆን አሳሳቢ ችግር ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
የዋዳኒ ፓርቲው እጩ አብዱራህማን መሀመድ ስልጣን የሚይዙ ከሆነ ከሶማሊያ መንግስት ጋር እንደሚደራደሩ ቃል ገብተዋል። ባለፉት 11 አመታት በታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ያገለገሉት አብዱራህማን ከሶማሊያ ጋር ለመደራደር ተሞክረው የከሸፉ ድርድሮችን ዳግም አስጀምራለሁ ነው ያሉት፡፡
ከፍትህ እና እድገት ፓርቲ ሶስተኛው እጩ ዋራቤ በበኩላቸው በሶማሊላንድ ብሔራዊ አንድነቱ የተጠበቀ መንግስት በመመስረት የሀገርነት እውቅናን አስገኛለሁ ብለዋል፡፡
የዚያድ ባሬ መንግስት በ1991 መውደቅን ተከትሎ ከሰሜን ምዕራብ ሶማሊያ ክፍል የተገነጠለችው ሶማሊላንድ ዘንድሮ የምታደርገው ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው መረጃ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ለሚቀጥሉት አምስት አመታት የሚያስተዳድሯቸውን መሪዎች ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣብያዎች ያቀናሉ፡፡