አሜሪካ በመላው ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲታወጅ ጠየቀች
ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር ለመጀመር የታጠቁ ሃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ጥሪ አቅርባለች
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ የሚገኘውን የአሜሪካ ግቢ ጎብኝተዋል
አሜሪካ በመላው ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲታወጅ ጠየቀች።
የተኩስ አቁም አዋጁ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን በንግግር ለመፍታትና ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር ለመጀመር ፈር እንደሚቀድም ነው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ የተናገሩት።
አምባሳደር ማሲንጋ በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ የሚገኘውን የአሜሪካ ግቢ ጎብኝተዋል።
አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም የአሜሪካ ግቢ ከ87 አመት በፊት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ከሞት ማምለጫ መሆኑን አውስተዋል።
የካቲት 12 1929 ፋሺስት ጣሊያን በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት ጭፍጨፋ ሲፈጽም አሜሪካዊው ዲፕሎማት ኮርኔልስ ቫን ኤንገርት ከ750 በላይ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲው ውስጥ እንዲደደበቁ ማድረጋቸውን በመጥቀስ።
ኢትዮጵያውያውያን ከ87 አመት በፊት የሰውነት ክብራቸው ተጥሶ በህይወት የመኖር መብታቸው ሲነጠቅ ታይቷል ያሉት አምባሳደሩ፥ የሞራል ልዕልና እና ሰብአዊነት ካላቸው ኮርኔልስ ቫን ኤንገርት ልንማር ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል።
ከ87 አመት በኋላም በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት የሰው ልጆች ክብር እና በህይወት የመኖር መብት በታጣቂዎች፣ ዘራፊ ቡድኖች እንዲሁም በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መጣሳቸው መቀጠሉ ከታሪክ አለመማራችን ያሳያል ብለዋል።
በጦርነት እና ግጭት ወቅት ጭምር የሰው ልጆች ክብርና ሰብአዊ መብት ሊከበርና ሊጠበቅ እንደሚገባ በማሳሰብም ኢትዮጵያውያን ካለፈ ታሪካቸው ሊማሩ ይገባል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶችንም በንግግር መፍታትና ንጹሃንን ከጉዳት መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የታጠቁ ሃይሎች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በንግግር ከመፍታት ይልቅ ጦር መስበቃቸውና መንግስት ይህን ለማስቆም የሚወስዳቸው እርምጃዎች መጠንከር የውይይት በሩን እየዘጋው እንዳይሄድም ስጋታቸውን አክለዋል።
የንጹሃን ግድያ፣ ያለህጋዊ አግባብ የሚፈጸም እስርና መሰወር እንዲሁም ከግጭቶች ጋር የተያያዙ አስገድዶ መድፈር መበራከት በአፋጣኝ እንዲቆምና በሽግግር ፍትህ አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑም ነው ያሳሰቡት።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳሰው የኦሮሚያ ነጻነት ሰራዊት (መንግስት ሸኔ እያለ የሚጠራው) በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከመንግስት ጋር ጀምሮት ወደነበረው ድርድር እንዲመለስ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ጠይቀዋል።
አምባሳደሩ ለፋኖ ታጣቂዎች ባስተላለፉት መልዕክትም "የንግግር በር መዝጋት አይጠቅማችሁም" ያሉ ሲሆን፥ ለድርድር ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ህወሃትም ከአማራ ክልል ጋር የሚወዛገብባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ በንግግር መፍታት እንጂ ሃይል አማራጭ እንደማይሆን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገባችበትን ችግር ለመፍታት ብሄራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህን ማስፈን ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስም አሜሪካ ለዚህ ጥረት ድጋፏን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር ለመጀመርም በመላ ሀገሪቱ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲታወጅና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ነው የጠየቁት።
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሼ አደራጃለሁ" የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ገደማ ጊዜ ቀርቶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከቀናት በፊት በባህርዳር የአባይ ድልድይ ሲመረቅ ለታጠቁ ሃይሎች የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።