ስፖቲፋይ ከ1 ሺህ በታች አድማጭ ያላቸውን ሙዚቃዎች ከክፍያ አገደ
በስፖቲፋይ ላይ ከተጫኑ 100 ሚሊዮን ሙዚቃዎች ውስጥ 60 በመቶዎቹ ከአንድ ሺህ በታች እይታ ያላቸው ናቸው ተብሏል
ሙዚቀኞች ኩባንያው ተገቢውን ክፍያ አይከፍልም የሚል ክሶችን እያቀረቡበት ነው
ስፖቲፋይ ከ1 ሺህ በታች እይታ ያላቸውን ሙዚቃዎች ከክፍያ አገደ፡፡
ከ15 ዓመት በፊት በስዊድን ስቶኮልም የተመሰረተው ስፖቲፋይ የሙዚቃ ማሰራጫ ተቋም አሁን ላይ ከ600 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አሉት፡፡
ከ100 ሚሊዮን በላይ ሙዚቃዎች የተጫኑበት ይህ ኩባንያ ከሰሞኑ አዲስ ህግ ይፋ አድርጓል፡፡
ከሚያዝያ 1 ጀምሮ ተፈጻሚ ሆናል የተባለው በዚህ አዲሱ ህግ መሰረት 1 ሺህ እና ከዛ በታች እይታ ወይም አድማጭ ላላቸው ሙዚቃዎች ክፍያ እንደማይከፍል አስታውቋል፡፡
በኩባንያው ላይ ከተጫኑ 100 ሚሊዮን ሙዚቃዎች ውስጥ አንድ ሺህ እና ከዛ በላይ እይታ ያላቸው ሙዚቃዎች 37 ሚሊዮን ያህሉ ብቻ ናቸው ሲልም አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ሙዚቀኞች ኩባንያው ተገቢውን ክፍያ ለድምጻዊያን አይከፍልም ሲሉ ወቀሳ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በሙዚቀኞች የቀረበበትን ክስ ውድቅ ያደረገው ስፖቲፋይ ኩባንያ ከ10 ሺህ በላይ ለሆኑ ሙዚቀኞች በዓመት 100 ሺህ ዶላር እና ከዛ በላይ እየከፈለ መሆኑን አስታውቋል፡፡
“የኢትዮጵያ የረቂቅ ሙዚቃ እናት” እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ አረፉ
በዳንኤል ኢኬ እና ማርቲን ሎሬንትዞን የተመሰረተው ስፖቲፋይ አሁን ላይ ዓመታዊ ገቢው ከ13 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ደርሷል፡፡
ስፖቲፋይ ካለው ከ600 ሚሊዮን በላይ ደንበኞቹ ውስጥ 236 ሚሊዮን ያህሉ ብቻ ክፍያ የሚከፍሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ነጻ አድማጮች ናቸው ተብሏል፡፡
ቴይለር ስዊፍትን ጨምሮ ሌሎች ድምጻዊያን ከዚህ በፊት ስፖቲፋይ ተገቢውን ክፍያ አልከፈለንም በሚል ሙዚቃዎቻቸውን ከዚህ ማጫወቻ ላይ ማውረዳቸው ይታወሳል፡፡
ኩባንያው ከሙዚቃ ባለፈም እንደ ፖድካስት እና መሰል አይነት የድምጽ ቅጂ ውጤቶችን ማጫዋት መጀመሩ ተጨማሪ ገቢ እና ደንበኞችን እንዲያገኝ እንዳስቻለው ተገልጿል፡፡