ድምጻዊ ሬማ በተለያዩ ሀገራት የያዛቸውን የሙዚቃ ኮንሰርቶች በጤና ምክንያት ሰረዘ
ድምጻዊው በኢትዮጵያ ለአዲስ አመት ዋዜማ በሸራተን ሆቴል ይዞት የነበረው ኮንሰርት መሰረዙ ይታወሳል
ከሰሊና ጎሜዝ ጋር የዘፈነው "ካልም ዳወን" የተሰኘው ዜማ በርካታ ሽልማቶችን አስገኝቶለታል
ድምጻዊ ሬማ በተለያዩ ሀገራት የያዛቸውን የሙዚቃ ኮንሰርቶች በጤና ምክንያት ሰረዘ።
ታዋቂው የአፍሮ ስልተምት ሙዚቀኛ ሬማ በጤና ምክንያት በተለያዩ ሀገራት የነበሩትን የሙዚቃ ድግሶችን ሰርዟል።
ድምጻዊው በኢንስታግራም ገጹ ላይ እንዳስታወቀው " የጤናዬን ጉዳይ ችላ ብዬ ቆይቻለሁ፣ አሁን ወደ ጤናዬ የማተኩርበት ወቅት ነው" ብሏል።
ድምጻዊው አክሎም እየተጠናቀቀ ያለው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት በተለያዩ ሀገራት በተከታታይ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ያዘጋጀበት ዓመት እንደነበርም ተናግሯል።
ይሁንና በታህሳስ ወር ውስጥ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የተዘጋጁ የፈረንጆች ገና እና አዲስ ዓመት የሙዚቃ ኮንሰርቶችን እንደሰረዘ ድምጻዊው አስታውቋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ድምጻዊው አክሎም " ከእረፍት በኋላ በአዲሱ ዓመት በአዲስ ጉልበት እንገናኛለን" ሲል ለደጋፊዎቹ እና አድናቂዎቹ ገልጿል።
ከታዋቂዋ አሜሪካዊ ድምጻዊት ሰሊና ጎሜዝ ጋር ያዜመው "ካልም ዳወን" የተሰኘው ሙዚቃ በአፍሪካ ሙዚቃ ታሪክ ብዙ ሪከርዶችን መያዝ ችሏል።
ይህ ዜማ በብዛት የታየ፣ የተጋራ እና ብዙ የተሸጠ የአፍሪካ ሙዚቃ በሚል ከምርጥ 100 የቢልቦርድ ሙዚቃ ደረጃዎችን በመያዝም አዲስ ሪከርድ አስመዝግቧል።
ድምጻዊ ሬማ በጤና ምክንያት የሙዚቃ ኮንሰርቶችን መሰረዙን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ሲሆን ሌላኛው ናይጀሪያዊው ድምጻዊ ዴቪዶ በቶሎ እንዲያገግም መልካም ምኞቹን ገልጾለታል።
ቴዲ አፍሮ የመላው አፍሪካ ሙዚቃ ሽልማት ምርጥ የሬጌ ሙዚቃ ሽልማትን አሸነፈ
ድምጻዊ ዴቪዶ አክሎም " የሰራኸው ስራ ከአካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ አንጻር ቀላል አልነበረም፣ በስራዎችህ አፍሪካን እና አለምን አኩርተሀል፣ እረፍት አድርግ እና ተመለስ" ሲል ጽፏል።
ይህ ናይጀሪያዊ ሙዚቀኛ ከሶስት ወራት በፊት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የሙዚቃ ስራዎቹን እንደሚያቀርብ ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ቢሆንም ዝግጅቱ መሰረዙ ይታወሳል።
ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት የተሰረዘው ድምጻዊው ከክርስትና ሀይማኖት ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ያልተገባ አስተያየት ሰጥቷል በሚል እና ከዚህ ጋር ቡተያያዘ ምክንያት ነበር።