ፕሬዝዳንት ጎታብያ ራጃፓክሳ ሀገሪቱን ለ20 ዓመታት መርተዋል
ስደት ላይ የሚገኙት የስሪላንካው ፕሬዝዳንት ጎታብያ ራጃፓክሳ በድጋሚ ወደ ሌላ ሀገር ሊሰደዱ መሆኑ ተገለጸ።
ሀገራውን ለቀው ማልዴቪስ የገቡት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ደግሞ ወደ ሲንጋፑር ለመሰደድ ማሰባቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል። ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸውን ጥለው ስደት ውስጥ የገቡት በተነሳባቸው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ነው።
ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ስሪላንካውያን ቤተ መንግስት ሆነው ደስታቸውን ሲገልጹ እርሳቸው ደግሞ ወደጎረቤት ሀገር ተሰደዋል።
የማልዴቪስ መንግስት፤ ስልጣን የለቀቁት የስሪላንካ ፕሬዝዳንት ወደ ማልዴቪስ እንደመጡ አረጋግጦ ነበር። ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ ወደ ማልዴቪስ መግባታቸውን የሀገሪቱን መንግስት የገለጸ ሲሆን ወደ ሌላ ሀገር የማቅናት እቅድ እንዳላቸውም ጠቁሞ ነበር።
ፕሬዝዳንት ጎታብያ ራጃፓክሳ ዛሬ በግል ጀት ወደ ሲንጋፑር እንደሚገቡ ይጠበቃል። ምንም እንኳን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በስደት ላይ ቢሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት በመሆን ራሳቸውን ሰይመዋል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ጎታብያ ራጃፓክሳ ስሪላንካን ለ20 ዓመታት የመሩ ቢሆንም አሁን ግን ስደት ላይ ናቸው። በ22 ሚሊየን ህዝብ ያላት ስሪላንካ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር የገጠማት ሲሆን ነዳጅን ጨምሮ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች እጥረት አጋጥሟታል።
ለአንድ ዓመት 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ በጀት የሚያስፈልጋት ቢሆንም አሁን ላይ የሀገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ መጠን እጅግ መሟጠጡ ተገልጿል።