በሺዎች የሚቆጠሩት ተቃዋሚዎች የፕሬዝዳንቱን መኖሪያ ቤት ሰብረው መግባታቸው ተነግሯል
የስሪላንካ ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓከሳ በገጠማቸው ከባድ ተቃውሞ ምክንያት መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ሸሹ፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩት ተቃዋሚዎች የፕሬዝዳንቱን መኖሪያ ቤት ሰብረው መግባታቸው ተነግሯል፡፡
መኖሪያ ቤቱን የሚጠብቁ የጸጥታ አካላት ተቃዋሚዎቹን ለማስቆምና በአስለቃሽ ጭስ ለመበተን ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
የእስያዋ ስሪላንካ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት በህዝባዊ አመጽ እየተናጠች ሲሆን የኑሮ ውድነት አማሮናል ያሉ ተቃዋሚ ዜጎች የፕሬዝዳንቱን መኖሪያ ቤት ተቆጣጥረዋል፡፡ ሆኖም ምንም ዐይነት የንብረት ጉዳት አለማድረሳቸው ነው የተነገረው፡፡
የሀገሪቱ ፖሊስ የተቃዋሚዎችን ድርጊት ለመቆጣጠር ቢሞክርም ተቃዋሚዎች የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ መኖሪያ ቤታቸውን ጥለው መውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፖሊስ የ73 ዓመቱን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ለደህንነታቸው በሚል ወዳልታወቀ ስፍራ እንዳዛወራቸው የገለጸ ሲሆን ህዝባዊ ተቃውሞው መቀጠሉን ተከትሎ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ ተሰግቷል፡፡
የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔያቸውን ለአስቸኳይ ስብሰባ የጠሩ ሲሆን በህዝቡ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ከስልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ ላይ ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ የምክር ቤት አባላትን ለአስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠሩ ማዘዛቸውም ነው የተነገረው፡፡
22 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ስሪላንካ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር የገጠማት ሲሆን ነዳጅን ጨምሮ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ከፍተኛ እጥረት በማጋጠሙ ህዝቡ ወደ አደባባይ ከወጣ ወራትን አስቆጥሯል፡፡
ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ከፈረንጆቹ 1948 ጀምሮ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን ችግሩን ለመቋቋም መቸገሯ ነው የተገለጸው፡፡
ለዜጎቿ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድሃኒቶችን መሰል መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማቅረብ ተቸግራለችም፡፡
ለአንድ ዓመት 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ በጀት የሚያስፈልጋት ቢሆንም አሁን ላይ የአገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ መጠን እጅግ መሟጠጡ ተገልጿል፡፡
በዚህም የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ጨምሮ ጎረቤት ሀገራትን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራትን ደጅ ብትጠናም ለችግሯ መፍትሄ የሚሰጣት ሀገርም ሆነ ተቋማት እስካሁን አልተገኘም፡፡