ተቃዋሚዎቹ ወደ ሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሰብረው መግባታቸው ተነግሯል
ፕሬዝዳንት ራጃፓክሳ ሸሽተው ማልዲቭስ መግባታቸውን ተከትሎ ስሪላንካን በጊዜያዊነት እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክረምሲንግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዋጁ፡፡
አዋጁ በመላ ሃገሪቱ የሚተገበር ነው የተባለ ሲሆን በምዕራዊ የሃገሪቱ አካባቢ ሰዓት እላፊም ተጥሏል፡፡
ሆኖም ከአሁን ቀደም የፕሬዝዳንት ራጃፓክሳ መኖሪያ ቤትን የተቆጣጠሩት ለውጥ እንፈልጋለን ባይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አሁንም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ቢሮ ለመግባት አመጽ ላይ መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡
ይህን ተከትሎም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክረምሲንግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁት፡፡ በአዋጁ ለማመጽ የሚሞክር የትኛውም አካል በቁጥጥር ስር እንዲውልና እንዲታሰር ተቃዋሚዎች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱባቸው ተሽከርካሪዎች እንዲያዙም ታዟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖሊስ እና የሃገሪቱ መከላከያ ህግና ስርዓትን እንዲያሰፍኑ ነው በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በተላለፈ መልዕክታቸው ያዘዙት፡፡
ይህን ለማስፈጸም የሚችል ከመከላከያ እና ፖሊስ እንዲሁም ከሌሎች የመንግስት አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ መዋቀሩንም ነው የተናገሩት፡፡
ሆኖም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተቃውሞውን ያረግበው ይሆን ወይ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
ስለ ሁኔታው በመዘገብ ላይ ያሉ የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎችም ተቃዋሚዎች ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሰብረው መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቃዋሚዎቹ ቀደመ ሲል የጠቅላይ ሚኒስትሩን የግል መኖሪያ መቃጠላቸው ይታወሳል፡፡
ኤ.ኤፍ.ፒ ደግሞ ተቃዋሚዎቹ የሃገሪቱን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመቆጣጠር ሙከራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጭምር ነው የዘገበው፡፡
ፕሬዝዳንት ራጃፓክሳ ሸሽተው ማልዲቭስ ቢገቡም በሃገሪቱ የሚገኙ የስሪላምካ ዜጎች ተላልፈው ለሃገራቸው እንዲሰጡ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡